Skip to main content

የብጹዕ አቡነ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ መልእክት

20.03.2020 Top news
የብጹዕ አቡነ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ መልእክት

 "በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ" ዘጽ ም.23 ቁ. 25

ዓለማችን ያለወትሮዎ አዝናለች ቆዝማለች፡፡ በሀገራችን ብሎም በዓለማችን የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ(COVID-19) ዓለማችንን ለድንጋጤና ለጭንቀት ዳርጓታል፡፡ እስካሁን ድረስ ባላው የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት መረጃ መሠረት በሁለት መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፤በሺዎች የሚቆጠሩ ላይመለሱ እስከወድያኛው አሸልበዋል፤ በየቀኑ የሚያዙ ሰዎች የቁጥር አሀዝ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ የቫይረሱ ባህርይ ሙሉ በሙሉ በባለሙያዎች ጥናት ያልተደረሰበት መሆኑ ችግሩን ውስብስብ አድርጓታል፡፡ የበሽታውን አሳሳቢነት ከፍ የሚያደርገው የስርጭቱ ፍጥነት እና መድሃኒት አልባ መሆኑ ሲሆን የቫይረሱ ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ ዓለማችንን የደካማ ምጣኔ ሁብት፤ የጤና ቀውስ ፤ የስነ ልቦና ጫና እና የተወሳሰበ የማኅበራዊ ግንኙነት መገለጫ ትሆናለች፡፡

በሽታውን ለመከላከል ከኛ ምን ይጠበቃል?

ወረርሽኙን በፍርሃት ሳይሆን በእውቀት (በመረጃ) በጭንቀት ሳይሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ላይ በመደገፍ ልንከላከለው ይገባል፡፡ ይኽም የእግዚአብሔርን ድርሻ ለሱ ሰጥተን የራስን ድርሻ መወጣት ግድ ይለናል፡፡  እግዚአብሔር ንጹሐ ባህርይ ስለሆነ አደፍ ጉድፍ አይስማማውም፡፡ የሱ ፍጥረት የሆን እኛም እሱን ከምንመስልበት መንገድ አንዱ በንጽህና  እና በቅድስና መኖር ሲሆን የነፍስ ንጽህና ለሰማያዊ ቤታችን የስጋ ንጽህና ደግሞ ለምድራዊ ቤታችን አስፈላጊያችን  ናቸው፡፡ መጽሐፍ “በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ” መጽ. ኢዮብ ም. 22 ቁ. 30 ማለቱ በአንድ በኩል ከመጥፎ ተግባር እጆቻችን ተቆጥበው መኖር እንዳለባቸው ሲያስተምረን በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ዘመን የመጣውን በሽታ ልንሻገረው የምንችለው የግል ንጽህናችንን በመጠበቅ መሆኑን ሲያጠይቀን ነው፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን ልጄ ሆይ “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል ማስተዋልም ይጋርድሃል” ምሳ ም.1 ቁ 11 በማለት በጥንቃቄ የምንመላለስ እና የባለሙያዎችን ምክር በአግባቡ የምንፈጽም ከሆነ ከመጣው ጥፋት እንደምንድን ይነግረናል፡፡

በሌላ መልኩ ወቅቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የምናጠብቅበት በንስሐ እና  በእንባ ወደ እሱ የምንመለሰበት ነው፡፡ የሰው ልጅ እንጂ እግዚአብሔር ለቃሉ ታማኝ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ብታመልኩት እህል ውኃውን  እባርክላችኋለው በሽታንም ከመካከላችሁ አርቅላችኋለሁ ዘጽ ም.23 ቁ. 25 ሲል የተናገረው ቃል ዛሬም አማናዊ ነው፡፡ ብንታመም እንኳን በእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት ጤናችንን ሊመልስልን ደዌአችንን ሊፈውስልን የታመነ አምላክ መሆኑን “እኔ ጤናህን እመልስልሃለሁ ቁስልህንም እፈውሳለሁ”ትን ኤር ም. 30 ቁ. 17 ሲል በነብዩ አንደበት ተነግሮናል፡፡

ራሱ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ሠርቶ ለጨረሰው ለሰሎሞን ሕዝቡ በምሕላና በጸሎት ቢመለስ ወረርሽኝና ተላላፊ በሽታዎችን ሊያስወግድለት ቃል ኪዳን እንዲህ ሲል ገብቶለታል፡- “ዝናብ እንዳይወረድ ሰማያቱን ብዘጋ  ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው  ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር (ተላላፊ በሽታ) ብሰድድ  በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ  ፊቴንም ቢፈልጉ  ከክፉ መንገዳቸው ቢመለሱ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ ”2 ዜና መዋ ም. 7፡13 -14 ፡፡የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር የእኛን ኅጢአት ሳይሆን የደጋግ አባቶቻችንን ጸሎት እና መግቢያ መውጫቸውን የማያቁትን የሕጻናትን የዋህነት ተመልክቶ መዓቱን በምሕረት፤ቁጣውን በትዕግስት ይመልስልን፡፡      

አሜን

                አባ ሳሙኤል 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

‹ Back to List