በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ የተደረገ ቃለ ምልልስ

ጥያቄ1፦ፅንስ ማቋረጥን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያላት አቋም  ምንድ ነው?

መልስ፦ ፅንስ ማቋረጥን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትቃወመ ዋለች፤አስተምህሮዋና ቀኖናዋም ይቃወማል። ምንያቱም፦ ፅንስ የሰው  ዘር በምድር ላይ እንዲበዛ እግዚአብሔር ስለፈቀደ ‹‹ብዙ ተባዙ አላቸው፤ ባረካቸውም›› (ዘፍ ፩፥፳፰) ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት የሚገኝ በረከት ነው፤ስለሆነም ፅንስ ገና ያልታየና ያልተወለደ ቢሆንም ከእግዚአብሔር ሕይወት የተሰጠው ፍጡር ነው። ‹‹ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ›› (መዝ.፳፩፥፱) ‹‹ከማሕፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፤ከእናቴ ሆድ ጀም መሸሸጊያዬ ነህ››(መዝ.፸፥፮) እንደተባለው ሁሉ ፅንስ የእግዚአብሔር ጥበቃና መግቦት ያለው ነው። እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ለወደፊት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ተልእኮ ያለው እንደሚሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ዕውቅና  የተሰጠውና የመኖር መብት ያለው ነው። ስለሆነም ከዚህ በላይ በተገለጸው    አምላካዊ ቃል መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፅንስ ማቋረጥን አጥብቃ ትቃወማልች።(ዘፀ. ፳፥፩፫)

 

ጥያቄ 2፡ ለእናቲቱ ለሕይወት አሰጊ በሆነ ደረጃ የሚገኝ ፅንስ እንዲቋረጥ ቢደረግ ምን ስሕተት አለው?

መልስ፦ አንዱን ሕይወት ለማዳን ሌላውን ሕይወት ማጥፋት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚደገፍ አይደለም። ሁሉንም ለማዳን የሚቻለውን ያህል ጥረት ማድረግ ሃይማታዊም ሰብአዊም ግዴታ ነው፤ ከሰው ዕውቀትና አቅም በላይ የሚይሆነውን ግን ሁሉን ማዳን ለሚቻለው አምላክ መተው  ነው እንጂ አንዱን ለማዳን ሌላውን መግደል የሚለውን ሐሳብ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም። ምክንያቱም ከላይ እንደተገለጸው፦

1.  ፅንሱ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ ዕውቅና ያለውና የመኖር መብት ያለው ሕያው ፍጡር ስለሆነ፥

2.  በሰው በኩል የሚቻለውን በሰው አማካይነት፥ ከሰው ዕውቀትና ዐቅም በላይ   የሆነውን በራሱ በአምላካዊ ሥልጣኑ ማዳን የሚቻለው እግዚአብሔር ብቻ ስለ ሆነ ነው።( ዘዳ. ፴፪፥፴፰፤ ፩ኛ ሳሙ፪፥፮)

ስለዚህ በመጀመሪያ ሴቶች ለመጽነስ ሲፈልጉ ሕገ እግዚአብሔር መጠበቅ ሕገ ተራክቦን ማክበር፤ ከዚያም ጤነኛና በትክክል የእርግዝና ሂደት ውስጥ የሚገኝ ልጅ እንዲሰጣቸው በጸሎት፤ በጾም፤ በሰጊድ፤ በምጽዋትና፤ በንሥሐ ፈጣሪን መጠየቅና ኀሊናን ማዘጋጀት ከተለያዩ ሱሶች ራስን መጠበቅ ይገባል። የተባረከና ጤነኛ ጽንስ አድርግልኝ መልካም  ልጅ ፈጣሪውን የሚፈራ፤ እናት አባቱንና ሰውን ሁሉ የሚያከብር ልጅ ስጠኝ ብሎ መለመን ይገባል። ይህ ደግሞ በወንዱም በሴቷም በኩል ሊደረግ የሚገባው ልመና ነው። በመሆኑም ሰዎች አስጊ ነው ያሉት ላይሆን ይችላል።ጤነኛ ነው ያለት ደግሞ ችግር ሲፈጥር ይታያልና በስጋት ብቻ ጽንስ እንዲቋረጥ፤ሕይወት እንዲጠፋ ማድረግ  ግን ተገቢ አይደለም።

ጥያቄ 3፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቤተሰቦችና ዘመዳሞቸ መካከል ጋብቻና ሩካቤ ተከለከለ መሆኑን ታምናልች። በአሁን ወቅት ግን በሀገራችን በቤተሰብና  በዘመዶቻቸው ተደፍረው የፀነሱ እንዳሉ የፖሊስና ሌሎች መረጃዎች ያመለክታሉ። እናም አንዲት ሴት በአባቷ ወይም በወንድሟ መደፈር ያጋጠማትን ፅንስ ብታስ ወርድ ወይም ብታቋርጥ ኃጢአቷ ምንድን ነው?

መልስበቅዱሳት መጻሕፍትና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከጋብቻና ከግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚከለክሉ፦የሥጋ ዝምደና፥ መንፈሳዊ ዝምድና (አበልጅነት)፥ የጋበቻ ዝምድና እና የማደጎ ዝምድና ናቸው። እነዚህ  የዝምድና ሕጎች እንዲጠበቁ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። እነዚህ የዝምድና ሕጎች ተሽረው ቢገኙ የዝምድና ሕጉን በሻሩ ወገኖች ላይ ቀኖናዊ ቅጣት ትወስናለች እንጂ ዝምድናውንና የዝምድናው ሕግ መሻሩን ሳያውቅ በአጋጣሚ በተፈጠረው ፅንስ ላይ የሚሰጥ የሞት ፍርድን ኦርቶዶክሳዊት  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ ትቃወ ማለች። ምክንያቱም ከላይ እንደተገለጸው ዝምድና በማፍረስ ከተፈጸመው ኀጢአት በላይ የበለጠ ነፍስ የመግደል ወንጀል መፈጸም ስለሚሆን ነው (ዘፀ.፳፥፩፫)። ስለዚህ ከዘመድ ተፀነሰ በሚል ሰበብ ፅንስ ማስወረድ ወይም ማቋረጥ በኀጢአት ላይ ኀጢአት መጨመር ነው።

ጥያቄ 4፡ሀገራችን ከላይ በተጠቀሰው በእናቲቱ ዘላቂ ጤንነትና ሌሎች አስገዳጅ በሆኑ ሁኔታዎች የሚፈጠርን ፅንስ ማቋረጥ እንደሚቻል በከፊል በሕጓ ተቀብላለች። በዚህ የቤተ ክርስቲያን ሐሳብ ምንድን ነው።

መልስ፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት መጻሕፍትና በቀኖናዊ አስተምህሮዋ አስቀድሞ በዝምድና መካከል የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዳይፈጸም፥ አሰገድዶ መድፈርና ያለዕድሜ ጋብቻ እንዳይኖር ታስተምራለች፥ ትከለክላለች እንጂ በማንኛውም ምከንያት ፅንስ ከተፀነሰ በኋላ የማስወረድና የማቋረጥ ተግባርን አትቀበልም። ስለዚህ የበደለ የበደለውን እንዲክስና እንዲቀጣ፥ የተበደለም ሊካስ እንደሚገባ የሚያመለክተውን ሕግ አጠናክሮ ተግባራዊ የሚያደርግ መመሪያ ማውጣት ሲገባ ምንም ያልበደለ ሕይወትን ማጥፋት ወንጀል አይደለም የሚል ሕግን ማውጣትንና ማወጅን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ ትቃወማለች። እንዲሁም በዝምድና መካከል በተደረገ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚለው ሁኔታ የሚፈጠር ፅንስንም ማቋረጥ ወይም ማስወረድ ወንጀል እንደማይሆን መገለጡ በሕገ ተፈጥሮም፥ በሕገ ሃይማኖትም የሚደገፍ አይደለም፤ምክንያቱም የጥፋት ውሳኔ ሊሰጥ የሚገባው የዝምድና ሕግን በተላለፉት ላይ እንጂ ምነም ሳያውቅ በተፈጠረ ፅንስ ላይ የሞት ፍርድ የሚፈቅድ ሕግ ማውጣት ትክክል ነው ብላ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ስለማታምን ነው።

ጥያቄ 5፡ ቤተሰብን ለመመጠን የሕክምና ሳይንስ የደረሰበትና በዓለም ሁሉ ተቀባይነት ያገኘው የፅንስ መከላከያ ኪኒን ወይም መርፌና ኮንዶም መጠቀምን ነው። በዚህ ላይ ቤተ ክርስቲያን ምን ትላለች?

መልስ፡ ይህንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፤ምክንያቱም‹‹ብዙ ተባዙ››(ዘፍ.፩፥፳፰) ያለውን የፈጣሪ ትእዛዝ መቃወም ስለሚሆን ነው። ስለሚሆን ነው። በተጨማሪም ተግባሩን እየፈጸሙ ፅንስ እንዳይሆን መከላከል የሚያስቀሥፍ ተግባር ነው። የይሁዳ ልጅ አውናን የተቀጠፈው በዚህ ተግባር ነውና (ዘፍ.፴፰፥፰-፲፩) ቤተክርስቲያን የወሊድ መከላከያን አትቀበለውም፤ምክንያቱም ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንደመሆናቸው (መዝ.፻፳፯፥፫‐፬) ፈቃደ እግዚአብሔርን መከላከል ነው፤ ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያናችን በዓመት ውስጥ ሰባት አጽዋማት እንዲሁም ሰንበታትን ጨምሮ ወርኀዊ በዓላት ስላሉ በእነዚህ ጊዜያት የግብረ ሥጋ ግንኙነት አይፈቀድም እንደሁም ቤተክርስቲያን እናቶች ልጆቻችውን ቢያንስ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት ሳያቋርጡ እንዲያጠቡ ስለምትመክር (፩ሳሙ.፩፥፳፪፥፳፬) በእነዚህ ጊዜያት እናቶች ልጆቻቸውን አራርቀው ሊወልዱ ይችላሉ።

ጥያቄ፡6 ከሕክምና ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት ሰዎች ከሞት በኋላ የዐይናቸውን  ብሌን እንዲሁም እንደ ኩላሊት የመሳሰሉትን የሰውነት ክፍሎች ለሌሎች በመለገስ ላይ ይገኛሉ። ይህን ጉዳይ በተመለከተ የኦቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አቋም ምንድን ነው።

መልስ፡ የሰውነት አካላት ልገሣ እና ንቅለ ተከላን በተመለከተ ይህን ዓይነት ገቢረ ሠናይ      የኢትዮጵያ ኦተቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አትቃወምም። ነገር ግን  ኩላሊት የሚለገሰው ለጋሹ በሕይወት እያለ ስለሚሆን ለጋሹን በማይጐዳ  መልኩ በለጋሹሙሉ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። ዐይን መለገስንም በተመለከተ ምንም እንኳ ለጋሹ ከሞተ በኋላ የሚደረግ ቢሆንም በሕይወት ሳለ በሚሰጠው ሙሉ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። በዚህ ዓይነት መልኩ የሚከናወን የአካል ክፍል ልገሳ ምግባረ ሠናይን፥  አፍቅሮ ቢጽን የሚገልጽና ሌላውን የማዳን መልካም ሥራ ስለሆነ ቅዱስት ቤተ ክርስቲያን አትቃወምም።(ዮሐ.፩፭፥፩፫- ገላ.፬፥፩፭)

ጥያቄ 7፡ መውልድ የማይችሉ ሴቶ በሌሎች ሴቶች ማሕፀን በኪራይ መልክ ልጅ ማግኘት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ተደረሷል። የህስ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ምን ምላሽ ይኖረዋል?

መልስ፡ ይህንም ከሕገ ተፈጥሮ ውጭ ስለሆነ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን      አትቀበለውም፤ምከንያቱም በሌላ ሴት ማሕፀን ተከራይታ ልጅ ለማግኘት የምትፈለገዋ ሴት የመነፅነስን፥ ዘጠኝ ወር በማሕፀን አርግዞ፥ በእትብት አምጦ የመውለድን  አጥብቶ የማሳደግ ጸጋ የማቃለልና በሌላ ሰው ድካም ልጅ ለማግኘት መፈለግ በሃይማኖት፥ በተፈጥሮ ሕግ፥ በኀብረተሰብ ባህልና ሞራልም የማይደገፍ ኢተፈጥሮአዊ ስለሆነ ነው።ማሕፀንዋን የምታክራየዋ ሴትም አምላክ በተፈጥሮ ባደላት አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት ባለው መሠረት አንድ       ወንድ አግብታ የራሷን ልጅ ፀንሳ  መውለድና ማሳደግ ሲገባት ማሕፀንዋን እንደ ግዑዝ ማኅደር በማድረግ ለገንዘብ ስትል ለሌላ ዘር ማከራየቷ በተፈጥሮ ያገኘችውን በራስ ፀንሶ የመውለድን ጸጋ የማቃለልና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ፍለጋ  ስለሆነ ይህን ቅዱስት ቤተ ክርስቲያን  አትደግፈውም።

ጥያቄ 8፡ ደም መስጠትና መቀበልስ?

መልስ፡ ደም የመስጠትና የመቀበል ተግባር ሕይወትን ለማትረፍና በሕይወት ለማቆየት የሚፈጸም ምግባረ ሠናይ ስለሆነ ቅዱስት ቤተ ክርስቲያን አትቃወምም። በመሆኑም በመጀመሪያ ደም ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል። ደም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳው የሥጋ ሕይወት (ነፍስ) በደም ውስጥ ነው የምትኖረው፤‹‹እስመ ደም ነፍሱ ውእቱ ለኵሉ ዘሥጋ ደም የሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ ነፍስ (ሕይወት )ነውና፤›› (ዘሌ.፲፯፥፲‐፲፬) ሕይወት ላላቸው እንስሳት ሁሉ የሕይወታቸው መሠረት ደም ነው፤የእንስሳት ሕይወት ደም ነፍስ የምትባል ስትሆን፥ የሰው ሕያዊት ነፍስም በደም እንደምታድር መጽሐፈ ኩፋሌ ያስረዳል።(ኩፋ.፯፥፰)

በመሆኑም ሕያዊት ነፍስ በሥጋ ውስጥ አድራ ሥጋን ሕያው የምታደርግበት ሰው ከሚመገበው እህልና ወኃ እየተጣራ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽ ንጥረ መባልዕት ነው። ስለዚህ በሕክምና ተግባር ደምን መለገስም ሆነ መቀበል የሚደገፍ መልካም ተግባር ነው። ይኸውም፡-

ሀ. ለመድኃኒትነት እንጂ ለምግብነት አይደለምና፥

ለ. የሰውን ሕይወት ለማትረፍ ደማችን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንም ቢሆን የመስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታ አለብንና፥

ሐ. በደም ለጋሽናም ሆነ በደም ተቀባይ ላይ የጤና ችግር በማያስከትል መንገድ የሚከናወን የበጎ አድራጎት ተግባር ነው፥

መ. በአርአያ እግዚብሔር ለተፈጠረ፥ የተፈጥሮ ወንድማችን ለሆነ የሰው ልጅ ሁሉ ያለንን ፍቅርና ርኀራኄ የሚገልጽ ተግባር ነውና  (ማቴ. ፲፱፥፲፱ ፤ ዮሐ. ፲፭፥፲፫)። ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር ለማንም የለውም ›› ከሚለው አምላካዊ ቃል አንጻር ሲታይ የሰውን ሕይወት ለማትረፍ የለጋሹ ጤንነት በማይጎዳ የሕክመና ጥበብ የሚደረግ የደምም ሆነ የሌሎች ክፍለ ሕዋሳት

ልገሳ የሚደገፍ የምግባረ ሠናይ ተግባር ነው፤ ስለዚህ ቅዱስት ቤተ ክርስቲያን ይህን አትቃወምም።

ጥያቄ 9 በቤተ ክርስቲያኗ አስተመህሮ ግብረ ሰዶም ኃጢአት እንደሆነ ይታወቃል በሀገራችን ግን ድርጊቱ ተስፋድቶ ይገኛል። ሁኔታው የቤተ ክርስቲያንዋን አስተምህሮ እየሸረሸረ አይመስለዎትም?

መልስ፡ ግብረ ሰዶማዊነት በብሉይ ኪዳን፥ በሐዲስ ኪዳን፥ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትና፥ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ የተወገዝ አስተጸያፊና አሰነዋሪ ተግባር መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ቅዱስት ቤተ ክርስቲያንም አጽንዖት ሰጥታ አስነዋሪነቱን፥ አስጸያፊነቱን፥ ኢተጥሮአዊና ኢክርስቲያናዊ ተግባር መሆኑን ታስተምራለች። ሕግ ተፈጥሮአዊውንና ሕግ መጽሐፍዊን ተላልፈው በሚያደርጉትም ላይ ደዌ ሥጋና ደዌ ነፍሰ፥ መቅሠፍተ ሥጋና መቅሠፍተ ነፍስ ታመጣለች (ዘፍ.፲፱፥፬-፴፰፤ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ እርስ በርሳቸው በክፍት የሚፈላለጉ፥ የሚያስተውሉ ፥ፍቅር የሌላቸው ፥ውል የሚያፈርሱ ምሕረት ያጡ ናቸው፥ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔር ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይሰማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም (ይላል የእግዚአብሔር ቃል) (ሮሜ፩፥፳፪‐፵፪) ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮዎች ሆኑ፣ ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚብሔር  በልባቸው ፍትወት ወደርኩስት አሳልፎ ሰጣቸው፣ ይህም  እውነት በውሸት ስለ ለወጡ፣ ስለዚህ የእግዚአብሔርም ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሲጣቸው፣ ሴቶቻቸውን ለባሕርያቸው፣በማይገባው ለውጡ፤ ወንዶችም ለባሕያቸው የሚገባውን ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባል ወደዱት መጣን ለማያረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤

በእነዚህ ላይ ዓመፃ ግፍ፣ መመኘት፥ ክፍት ፥ጉቦኝነት፥ ምንቀኝነት፥ ቅናትን፥ነፍስ መግደል፥ ክርክርን፥ ተነኰልን፥ ክፉ ጠባይን የሚያሾለከሱኩ፥ አእሙሮያቸው ተሞሉ፤ሐሜተኞች፥ አምላክንና የአምላክን ህግ የሚጠሉ፥ ትዕቢተሾች ትምክህተኞች፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር ይህንን እያስተማረች እየሰሙና እያወቁ በፈቃዳቸው ወደዚህ አስጸያፊ ተግባር ቢሄዱ ተግባራቸው የእነሱን ዐመፀኛነትና እልከኝነት ይገልጻል እንጂ የቅዱስት ቤተ ክርስቲያናችንን ተሰሚኒት የሚቀንስ አይደለም። ምክንያቱም ከእነዚህ ዐመፀኞች ይልቅ ሕገ ተፈጥሮንና ሕግ አምላክዊን ጠብቀው የሚኖሩ ወገኞች ይበዛሉና ነው።

ጥያቄ 10. ከኤች.አይ. ቪ. ቫይረስ ጋረ የሚኖሩ ወገኖች መድኃኒቱንና ፀበሉን አንድ  ላይ እንዲጠቀሙ ቤተ ክርስቲያኗ ልዩ አስተያየት ማድረጓ ይታወቃል፤ስለ ፅንስ ማቋረጥና የቤተሰብ ምጣኔ አስተምህሮዋን ወይም ዶክትራኗን ብታሻሽል ምን ችግር አለው?

መልስ፡ ቅድስት ቤተ ጸረ-ኤች አይ.ቪ.መድኃኒትን ከጠበል ጋር መውሰድ ከጽንስ ማቋረጥ እና ከቤተሰብ ምጣኔ ጋር በፍጽም አይዛምድም የመጀመሪያ ሕይወትን ለማዳን ሲሆን ሁለቱ ግን ተቃራኒውን መፈጸም ማለት ስልሆነ የሚሻሻል ነገረ የለም። ክርስቲያን የፈጣሪን ሕግ ተቀብላ ታስተምራለች እንጂ ቅዱስ ቃሉን የመቀነስ፥ የመጨመርና የማሻሻል ተግባርን አትፈቅድም። ምክንያቱም‹‹ብዙ ተባዙ››ያለውን አምላካዊ ትእዛዝ ማፍረስ ስለሚሆንና ሁለተኛም‹‹ነፍስ አትግደል›› ያለውን ማፍረስ ስለሚሆን ነው። (ዘፍ.፩፥፳፰፤ ዘፀ.፳፥፲፫)

ጥያቄ11. በሳይንስ ዓለም ነፍስ እንዳላች የሚያምኑና የማያምኑ ሳይንቲስቶች አሉ። እንደ ቤተ ክርስቲያን ነፍስ የሚባል ነገር አለ? ስለ መጠኗና ስለ ባሕርይዋ በሊቃውንት ወይም በመጽሐፍ የተሰጠ ማብራሪያ ካለ ቢያንስረዱን?

መልስ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማትሞት፥ የማትፈርስ፥ የማትበሰብስ ነፍስ በእያንዳንዱ ሰው እንዳላች ታምናልች የቅዱሳት መጻሕፍትንም ዋቢ አድርጋ ታስተምራለች። ስለ መጠኗ፦ ነፍስ ረቂቅ ስለሆነች መጠኗ ይህን ያህላል፥ ይህን ይመስላል ተብሎ ሊነገር አይችልም፤ ባሕርይዋ ግን፦ ለባዊት ( የምታስበ ) የምታስተውል ፥  ነባቢት (የምትናገር)፦ሕያዊነተ (የማተሞት) ለዘለዓለም ሕያው ሁና የምትኖር እንደሆነች በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን እንደሚከተለው እንመልከት)

‹‹እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፦ በፊቱ የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።››(ዘፍ. ፪፥፯)

‹‹ሥጋችሁን የሚያገድሉትን አትፍሩአቸው፥ ነፋሳችሁን ግን ሊገድሏት አይችሉም፤ ነገር ግን ነፍስንም ሥጋንም አንድ አድርጎ በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን እርሱን ፍሩት።››( ማቴ.፲፥፳፰)

ሐዋርያትም በአመክንዮ ‹‹የማትሞት ነፍስ በሥጋችን እንዳለች እናስተውል›› ብለዋል።(ሃይ.አበው ምዕ. ፮ ቁ. ፲፱) ይህን አምላካዊ ቃል መሠረት አድርጋ ቅዱስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የነፍስን ህልውና ታስተምራልች።

እነዚህ ሁለት ነገሮችም በዚህ ዓለም ያሉትን ፍጡራን የሚዛመድበት ሥጋ (ቁስ አካል) (material body) እና ከመንፈሳውያን ጋር አንድ የሚያደረገው ነፍስ ወይም መንፈስ (Soul or Spirit) ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስና መንፈስ አንዱን በአንዱ በመተካት መንፈሳዊውን ሁኔታ ልጅ የተፈጠረበትን ነገር (element) ይገለጸሉ። ሁለቱም ቃላት የሚወክሉት አንድ ነገር ነው። ይኸውም  የማይሞተውን የሰውን ነፍስ ነው። ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ እግዚአብሔርን ባመሰገነችበት ምስጋና መረዳት ይቻላል። “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኔቴ ሐሤት ታደርጋልች” መንፈሴ ኀሊናዬ ሁለንተናየ ማለት ነው። (ሉቃ ፩፥፵፮‐፵፯)። የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይቀድሳችሁ ነፍሳችሁን መንፈሳችሁንና ሥጋችሁንም (፩ ተሰሎ. ፭፥፳፫) የኢዮብም ንግግር “እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ…” እንዲል። (ኢዮብ.፳፯፥፫) መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስና ነፍስን ጐን ለጐን አንድ ዐይነት መልእክት ለማስተላለፍ በአንድ ጊዜ ይጠቅሳቸዋል። ጌታችነና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ስለ መዋቲ ሥጋ ሲናገር “ስለዚህ እላችኋላሁ ስለነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት ወይም ስል  ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ብሏል።(ማቴ.፮፥፳፭)። እዚህ ላይ ስለነፍሳችሁ ያለው ረቂቁን ወይም የማይሞተውን ነፍስ ለማለት ሳይሆን ሥጋን የሚመለከት ነው። ስለ ሥጋ ለመናገር ነፍስ የሚልበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በብዙ  ቦታ ተገልጿል።ነፍስ በሥጋ ስለምታድርና ሥጋን ስለምታንቀሳቅስ ስለ ሥጋ ለመናገር ሲፈልግ ነፍስ ይላል። በዙሁ ወንጌል ላይ ደግሞ ነፍስንና ሥጋን ለይቶ የእያንዳንዱን ባሕርያቸውን ጭምር ተናግሮአል። “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ።” እንዳለ።(ማቴ.፲፥፳፰) አቤቱ ነቢያትህን ገደሉ መሠዊያችንም አፈረሱ እኔም ብቻዬን ቀረሁ ነፍሴም ይሿታል። (ሮሚ ፩፲፥፫።) አንዳንዴም መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ሰውነትን  (ነፍስንና ሥጋን) በነፍስ ተክቶ ይናገራል። “የሕፃኑም  ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና።…”(ማቴ.፪፥፳)። እዚህ ላይ የሕፃኑን ነፍስ የሚለው ራሱ ሕፃኑን ሙሉ አይደለም እንዲሁም “ኢትቅትል ነፍሰ” እንዲል ነፍስ አትግደል ሲል ነፍስ የምትሞት ሆና አይደለም ለሥጋ ሰጥቶ መናገሩ ነው።“ዳይኮቶሚስቶች፤ ትራይኮቶሚስቶች” የሚያቀርቡትን  ፍልስፍናዊ ዘይቤዎችና ሳይንሳዊ አባባሎችን የተለያዩ መረጃዎች ትርጉማቸውንና ሐሳባቸውን የእግዚአብሔር ቃል  ውድቅ ያደርጓቸዋል።

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org