ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የእናቶችና ሕፃናት ሥርዓተ ምግብ እንዲሻሻል የተዘጋጀውን የሥርዓተ ምግብ የስብከት መመሪያ መረቁ፡፡
ይህም ለነፍሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች ትኩረት በመስጠትና እናቶችና ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በአጽዋማት ጊዜ ስለሚኖራቸው አመጋገብና ስለ ሥርዓተ - ምግብ ለማስተማር የተዘጋጀ ነው፡፡


አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ ጥቅምት 20 ቀን 2008 ዓ/ም - በዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትርያርክ ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሥርዓተ ምግብ ስብከት መመሪያን መረቁ፡፡ የሥርዓተ-ምግብ ስብከት መመሪያው ዋና ዓላማ እናቶችና ሕጻናት በመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት (ማለትም እናቶች ከፀነሱበት ጊዜ ጀምሮ ሕጻናት ተወልደው 2 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ)፤ በተለይም በአጽዋማት ጊዜ ጥሉላት (የእንስሳት ተዋጽዖ) ምግቦችን እንዲመገቡ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ የስብከት መመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት/ኤንጂን ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ የእናቶች የምግብ አለመመጣጠንና የሕጻናት መቀንጨር ችግርን ለመቅረፍና ለእናቶችና ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብና የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦችን መመገብ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ለመስጠት የተዘጋጀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ለዘመናት ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶችንና ዕድሜያቸው ከ 7 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እንዳይጾሙ ቢያዝም ብዙ ምእመናን ስለዚህ ጉዳይ በቂ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያ 7 የሕግ አጽዋማት ሲኖሯት፤ በድምሩ በዓመት ወስጥ ለ6 ወራት ተኩል ጊዜያት ሌሎች መንፈሳዊ ምግባራት መተግበርን ጨምሮ የእንስሳት ተዋጽዖ (ጥሉላት) ምግቦችን መመገብ አይፈቀድም፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮችና ምእመናን ይህንን መሠረት በማድረግ እንዲጾሙ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦችን ባለመመገብ ምክንያት በእናቶች ላይ የሚከሰተውን የምግብ አለመመጣጠን እና የሕጻናት መቀንጨር ችግርን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት/ኤንጂን ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ከቤተክርስቲያኒቷ መሪዎችና ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋር ሁለት ስብሰባዎችን በማድረግ፤ እናቶችንና ሕጻናትን በተመለከተ ስለ አጽዋማት ለማብራራትና በሥርዓተ-ምግብና ጾም ዙሪያ ያሉትን መመሪያዎችን በትክክል ለማስረዳት የሥርዓተ-ምግብ የስብከት መመሪያ አዘጋጅተዋል፡፡ የሥርዓተ ምግብ የስብከት መመሪያውም በየአኅጉረ ስብከት፣ ወረዳዎች፣ አጥቢያ ቤተክርስቲያን፣ ሰንበት ት/ቤቶች፣ ነገረ መለኮት ኮሌጆች፣ ካህናት ማሠልጠኛ ተቋማት እና ምእመናንንና ካህናትን ለማስተማር የሚያገለግል ነው፡፡
የስብከት መመሪያው በሚከተሉት አራት ዋና ዋና ቁልፍ ርእሶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን እነርሱም እንደሚከተሉት ቀርበዋል ፡፡
1. የነፍሰጡር እናቶች የአጽዋማት ጊዜ አመጋገብ፤
ሀ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ነፍሰጡር እናቶች በማኅጸናቸው ልጆቻቸውን ለ275 ቀናት (ወይም ለ9 ወር ከ5 ቀን) እንደሚሸከሙ ታውቃለች፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት ነፍሰጡር እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ መመገብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያኒቷ ነፍሰጡር እናቶች ከጸነሱበት ጊዜ ጀምሮ እስከሚወልዱ ድረስ የእንስሳት ተዋጽኦን ጨምሮ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ ትፈቅዳለች፡፡ ይህንንም መመሪያ ካህናት ለነፍሰጡር እናቶች እና ለምእመናን ማስረዳትና እንዲተገብሩትም ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡
2. የሚያጠቡ እናቶች የአጽዋማት ጊዜ አመጋገብ፤
ሀ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚያጠቡ እናቶች ለሁለት እንደሚመገቡ (ማለትም ለራሳቸውና ለጽንሱ) ታውቃለች፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት የሚያጠቡ እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ መመገብ ስለሚያስፈልጋቸውና ከእነርሱ የሚወለዱ ሕጻናት የመጪው ትውልድ ተረካቢ እንደመሆናቸው መጠን ጤናማ እድገት እንዲኖራቸው ቤተክርስቲያን የሚያጠቡ እናቶች የእንስሳት ተዋጽኦን ጨምሮ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ ትፈቅዳለች፡፡
3. የመመገቢያ ዕቃዎችና ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት አመጋገብ
ሀ. በአጽዋማት ጊዜ የማብሰያና የመመገቢያ ዕቃዎች በውሃ ታጥበው ስለሚጠሩና ደጋግመን ስለምንጠቀምባቸው ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በዚህ ሰበብ በአጽዋማት ጊዜ የእንስሳት ተዋጽዖ ምግቦችን እንዳይበሉ መከልከል የለባቸውም፡፡
ለ. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ዕድሜያቸው ከሰባት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ጤናማ እድገት እንዲኖራቸው ቤተክርስቲያን እንዳይጾሙ ደንግጋለች፡፡ ስለዚህም በአጽዋማት ጊዜ የሃይማኖት አባቶች ለቤተሰቦች (ማለትም ለእናቶች፣ ለአባቶችና ለአያቶች) ልጆቻቸውን የተመጣጠነ ምግብ፣ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦችን እንዲመግቧችውና እንዲንከባከቧቸው ማስተማር ያለባቸው መሆኑን ቤተክርስቲያን ታዛለች፡፡

                        

4. የሃይማኖት አባቶች፣ የባሎች እና የአያቶች ድርሻና ኃላፊነታቸው
ሀ. የሃይማኖት/የነፍስ አባቶች በነፍስ ልጆቻቸው ላይ ኃላፊነት ስላለባቸው ነፍሰጡር እናቶችን፣ የሚያጠቡ እናቶችንና አያቶችን በመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ወቅት ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ልዩ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸውና ልጆቻቸውን የተለያዩ በቫይታሚን የበለፀጉ ምግቦችንና በተለይም የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦችን እንዲመግቧችው ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ቤተክርስቲያን ታዛለች፡፡
ለ. ባሎች እና አያቶች የቅርብ የቤተሰብ አካል እንደመሆናችው መጠን ቤተሰቦቻቸውን (ማለትም ነፍሰጡር ሴቶችን፣ የሚያጠቡ እናቶችንና ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናቶቻቸውን) መመገብና መንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ስለሆነም በመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ወቅት የተመጣጠኑ ምግቦችን፣ በተለይም የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦችን በማቅረብና እነዚህን ምግቦች እንዲመገቡ ማበረታታት አለባቸው፡፡ ባሎች እና አያቶች በቤት ውስጥ ነፍሰጡር ሴቶችና የሚያጠቡ እናቶች ያለባቸውን የሥራ ጫና ለመቀነስ፤ ሥራም በመጋራትና ህጻናትን በመንከባከብ ሊያግዟቸው ይገባቸዋል፡፡
ሐ. ሊቃነ ካህናትና ሌሎች የቤተክርስቲያን አባቶችም ይህን በተመለከተ ለባሎችና ለአያቶች ትክክለኛ መመሪያ መስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ቤተክርስቲያን ታሳስባች፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ላይ የሥርዓተ-ምግብ የስብከት መመሪያው ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተሠራጨ ሲሆን እነርሱም በበኩላቸው የስብከት መመሪያውን በመላው ኢትዮጵያ በየአኅጉረ ስብከቱ እንደሚተገበር ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሥርዓተ-ምግብ ስብከት መመሪያው ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ በመላው አገር በ53ቱም አኅጉረ ስብከት ውስጥ ለሚገኙ ቀሳውስት፣ ሰባክያነ ወንጌል እና ዲያቆናት እንዲሰራጭ በማድረግና በእነርሱ በኩል በስብከት መመሪያው ውስጥ የተጠቀሱትን መልእክቶችና መመሪያዎች ለማኅበረሰቡ በስፋት እንዲዳረሱ ለማድረግ ቤተክርስቲያን የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም መመሪያዎችን ታስተላልፋለች፤ አስፈላጊው የጠባይ ለውጥ እንዲመጣም ቤተክርስቲያን በሚደረግላት ድጋፍ ስልጠና እንደምታካሄድ ለመግለፅ ትወዳለች፡፡ ይህ የሥርዓተ-ምግብ የስብከት መመሪያ በማኅበረሰቡ መካከል የሚታዩ ብዥታዎችን እና አሉባልታዎችን ለመቅረፍ ይረዳል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ፡-      Nutrition Sermon guide

ዘላለም መኩሪያ (ከዩ.ኤስ.ኤድ/ኢንጅን)፤+251911085613፣

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም 

ቀሲስ ሳምሶን በቀለ (ኢ.ኦ.ተ.ቤ)፤+251911639820፣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

                            

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org