የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አምስት ለጋሽ ሀገራት (አይርላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን እና ዩናይትድ ኪንግደም) በመጣመር ከመሠረቱት CSSP (Civil Society Support Program) ከተባለ እና በብሪቲሽ ካውንስል አስተባባሪነት ከሚመራው አጋር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአሶሳ ሀገረ ስብከት በካማሽ፣ አሶሳ እና ባምባሲ ወረዳዎች ላይ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያን እና ቫይረሱ በደማቸው ከሚኖር ወላጅ አጥ ሕጻናት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

 

በአሶሳ የሚገኘው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመምሪያው ውጤታማ ተብለው ከሚመደቡት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በግምባር ቀደምትነት የሚገኝ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካሉት 34 መንግሥታዊ ያሆኑ ድርጅቶች መካከል ው  ጤታማ ሥራ በማስመዝገብ አንደኛ በመውጣት ለሁለት ጊዜያት የዋንጫና የሠርተፊኬት ሽልማት አግኝቷል፡፡ ለሽልማቱ መገኘት ሀገረ ስብከቱ ዋነኛውን ሚና የተጫወተ ሲሆን ውጤቱ ለሌሎቹ አኅጉረ ስብከት አርአያ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ 

የሽመና ማምረቻ ቤት የተሠራበት ቦታ የክልሉ መንግሥት ለአሶሳ ሀገረ ስብከት ከሰጠው ቦታ ላይ ሀገረ ስብከቱ ለቤቱ ሥራ የሚውል ቦታ በነጻ የሰጠ ሲሆን ለቤቱ መሥሪያ እንዲሆን የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡ በተያያዘም ሀገረ ስብከቱ ለማምረቻው ቤት መብራት እና ውሃ በነጻ ያገባ ሲሆን ሠልጣኞች ለአንድ ዓመት በነጻ እንዲጠቀሙ ፈቅዷል፡፡   በተለይም ባለፉት 12 ወራት በብር 720,000 ዓመታዊ በጀት በባምባሲ ወረዳ ለሚገኙ 60 ተጠቃሚዎች የምግብ፣ የንግድ ክህሎት እና የዘመናዊ ሽመና ሥልጠናዎች ሲሰጥ ለሽመና ሰልጣኞች የሽመና ምርት ማምረቻ ቤት ሠርቶ ለሠልጣኞች አስረክቧል፡፡

በዘመናዊ የሽመና ሙያ የሰለጠኑ 15 የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ታኅሣስ 17 ቀን 2008 ዓ/ም በባምባሲ ወረዳ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አዳራሽ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡ ሰልጣኞቹ አካል ጉዳተኞች፣ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝ ወጣቶች፣ የአረጋውያን አሳዳጊዎች 11 ሴት እና 4 ወንዶች ናቸው፡፡ በሥፍራው በመገኘት ለሠልጣኞቹ የምስክር ወረቀት በመስጠት የመረቁት ቀሲስ ሳምሶን በቀለ፤ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽኑ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መምሪያ ኃላፊ ሲሆኑ እርሳቸውም የምስክር ወረቀቱን ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ሠልጣኞች በያዙት ወርቅ ሙያ ራሳቸውን ጠቅመው ቤተሰቦቻቸውን እና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙበት አሳስበዋል፡፡ የመንግሥት የልማት አጋር መሆኗን በመገንዘብ ሠልጣኞች ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ መሸጫ ቦታ እንዲያመቻቹላቸው፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩላቸው፣ ጥሬ ዕቃ የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ እና የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲያግዟቸው አደራ ብለዋል፡፡ በንግግራቸውም መጨረሻ CSSP ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ከእርሳቸው ቀደም ብሎም የአሶሳ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሊቀ መዘምራን ሐረገ ወይን ጫኔ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ሀገረ ስብከቱ ፕሮጀክቱ እንዲመጣ ያደረገውን ብርቱ ጥረት ገልጸው ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን የተሠሩ ሥራዎችን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ በዋነኝነትም ለሠልጣኞች ለተሠራው ቤት ሀገረ ስብከቱ የቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የባሙያ ወጪ የሸፈነ ሲሆን ከሚመለከታቸው የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በቅርበት ለመሥራት ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡     

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት መምህር ትህትና አበበ ስለፕሮጀክቱ አፈጻጸም ባደረጉት ገለጻ በፕሮጀክቱ ለ60 ተጠቃሚዎች እንደ ፍላጎታቸው ለእያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ 1.5 ኩንታል እህል እንደተሰጣቸው የፕሮጀክቱ የፋይናንስ አጠቃቀምም 99.91 በመቶ እንደሆነም ዘገባ አቅርበዋል፡፡ በሌላም በኩል ሠልጣኞች ያመረቱትን ምርት በመሸጥ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ብር 13,019 ማግኘታቸውን በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ በመጨረሻም በእንግዶቹ የዳቦ ቆረሳ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን የሠልጣኞች ምርትም ተጎብኝቶ የዕለቱ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡   በዕለቱ የተገኙትም አቶ መሐመድ አያሌው የቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካይ እንዲሁም አቶ ፋንታሁን መለሰ የክልሉ የልማት ጥምረት ሰብሳቢ በተከታታይ ፕሮጀክቱ በአነስተኛ በጀት የሚታይ ሥራ መሥራቱን አድንቀው ይህንንም ውጤታማ ሥራን በተመለከተ ጥምረቱ በየዓመቱ በሚያዘጋጀው መጽሔት ላይ በዝርዝር መውጣቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ፋንታሁን ንግግራቸውን በመቀጠል ለወደፊቱም አመርቂ ሥራ እያሳየ ከሚገኘው ከልማት ኮሚሽኑ ጎን እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል፡፡ ሌላው በዕለቱ የተገኙት የባምባሲ ወረዳ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ  ፈይሰል ዓሊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምታካሂደው የልማት ሥራ ደስተኛ መሆናቸውን ተናረው በተለይም ተጠቃሚዎቹን በሃይማታቸው ምንም ልዩነት ሳታደርግ በሰብአዊ ማንነታቸው ብቻ እንዲህ ዓይነት መልካም ሥራ በመሥራቷ ለሌሎች የእምነት ክፍሎች አርአያ መሆኗን ገልጸዋል፡፡ እርሳቸውም የወረዳው አስተዳደር ለሠልጣኞቹ ለምርት ሽያጭ የሚውል ግምባር የሆነ የመሸጫ ሱቅ በማፈላለግ በቅርቡ እንደሚሰጥ እና በገበያ ትስስር፣ በጥሬ ዕቃ አቅ  ርቦት እና ብድር በማመቻቸት ላይ ጠንክሮ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል፡፡ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የፕሮጀክት አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የባምባሲ ወረዳ ቤተክህነት ሊቀ ካህናት መልአከ ምሕረት  ገብረ መስቀል ባሕሩ አማካሪ ኮሚቴው የሠራቸውን ሥራዎች ሪፖርት በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org