በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በዱከም፣ በሰበታና በቡራዩ ከተሞች በዘላቂ የአካባቢና የግል ንጽሕና አጠባበቅ ላይ ከአከናወናቸው ሥራዎች መካከል በዱከም የተሠሩትን አስመረቀ፡፡

ኮሚሽኑ በሦስቱ ከተሞች በሚገኙ የገበያ ማዕከላት ለእያንዳንዳቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ባለስምንት ክፍል መጸዳጃ ቤቶች፣ ባለ አራት ከፍል የገላ መታጠቢያዎች፣ ከሠላሳ እስከ አርባ ሰው በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል አንድ ካፍቴሪያ፣ አንድ የባዮ ጋዝ ማብላያ እና አንድ አነስተኛ ሱቅ አሠርቷል፡፡ በተጨማሪም በሦስቱ ከተሞች በሚገኙ አራት ት/ቤቶች ለእያንዳንዳቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ባለአስር ክፍል መጸዳጃ ቤቶች፣ የእጅ መታጠቢያና አንድ አንድ የባዮ ጋዝ ማብላያ አሠርቶ አጠናቋል፡፡
የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ/ም በዱከመ ከተማ በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አግደዉ ረዴ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በመክፈቻ ንግግራቸዉም እግዚአብሔር መሬት፣ዉኃንና አየርን ፈጠሮ የሰዉ ልጅና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በአግባቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢያደርግም ፤ የተሰጠውን የተፈጥሮ ፀጋ ባግባቡ ሊጠቀም ባለመቻሉ ራሱን አደጋ ላይ ጥሎታል ብለዋል፡፡ ኮሚሽነሩ አያይዘው እንደተናገሩትም ሰዉ፣ እንስሳትና እጽዋት መሬትን፣ዉኃንና አየርን በመጠቀም ያድጋሉ፣ትዉልድንም ተክተው ያልፋሉ፡፡ በዚህ ዑደት ዉስጥ ሁሉም ሕይወት ያላቸዉ ፍጥረታት ጠቃሚና ጎጅ የሆኑ ቆሻሻ ነገሮችን ያመነጫሉ፡፡ ይህ ሒደት በአግባቡ ካልተያዘና በአግባቡ ካልተወገደ አካባቢን ከመበከሉም በተጨማሪ በሰዉ እና በሌሎችም ፍጥረታት ላይ የጤንነት ችግር እንደሚያስከትልም ኮሚሽነሩ አክለው ተናግረዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ ለኅብረተቡ ተደጋጋሚ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ በመደረጋቸው የአካባቢንና የግል ንጽሕናን ለመጠበቅ ተችሏል ሲሉ ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ዓላማውን ለማሳካት ላባረከቱት የመንግሥት አካላት፣ ለኔዘርላድድስ የልማት ድርጅት፣ ለአውሮፓ ኅብረት፣ ለመንግሥት አካላትና ለኅበረተሰቡ ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኮሚሽኑ የውኃ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደምመላሽ በበኩላቸው እንደተናገሩት በሦስቱም ከተሞች በሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች የሚኒ ሜዲያ መሣሪያዎች፣ ለግቢ ጽዳት እና ለጓሮ አትክልት ሥራ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ተሰጥተዋል፡፡ ሥራ የሌላቸውን ወጣቶች ከየከተማዉ የአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ማስፋፊያ ጽ/ቤት አማካኝነት በመመልመል አስፈላጊውን የሥራ ፈጠራ ክህሎት ሥልጠና በመስጠት የመነሻ ግብዓትና ቁሳቁሶችን በማቅረብ ከላይ በተጠቀሱት የፕሮጀክቱ አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ በመሥራት ራሳቸውንና ቤተ ሰቦቻቸውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ ኮሚሽኑ እየሠራ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ ገለጸዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት ግንባታ ከመቶ 75 የሚሆነው ከአዉሮፓ ኅብረት ቀሪዉ ደግሞ ከኒዘርላንድስ መንግሥት ልማት ድርጅት በተገኜ ገንዘብ በዱከም ከተማ ብቻ ወደ ብር 1.8 ሚሊዮን ፈሰስ መደረጉንም አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በልማት ኮሚሽኑ አስፈፃሚነትና አስተባባሪነት በቡራዩና በሰበታ ከተሞች ተመሳሳይ ሥራዎችን በመገንባት ላይ መሆናቸውንም ሓላፊው ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ 32,049 ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንና በፕሮጀክቱ የታቀዱ ሥራዎችን ለማስፈፀም 12.9 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እንደነበርም አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እነዚህን መሰል ፕሮግራሞች ለማከናወን አቅም ያለው መሆኑን የዱከም ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ እድሪስ፣ የአዉሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ጽ/ቤት ተወካይ አቶ አስናቀ አበራ፣ በኢትዮጵያ የኒዘርላንድስ የልማት ድርጅት ኃላፊ አቶ ወርቁ ቢሆነኝ እና በኒዘርላንስ ልማት ድርጅት የዚህ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋዲሳ ኃይሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org