የሴት ልጅ ግርዛት መጽሐፍ ቅዱስ የማያዘውና ቤተ ክርስቲያናዊ ሥርዓት ባለመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሙኤል

ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሐዲስ ኪዳንም ሆነ በብሉይ ኪዳን የሴት ልጅ ግርዛት እንዲፈፀም አልታዘዘም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ባላት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት መሠረት ድርጊቱን የማትቀበለውና የማትፈቅደው በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የልማ ኮሚሽኑ ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እንደተናገሩት ሴቶችን ለግርዛት አሳልፎ መስጠት እግዚአብሔር ለሴት ልጅ የሰጠውን የተፈጥሮ ፀጋ እንደመቃወም ይቆጠራል ፤ድርጊቱም የሀገሪቱን የተቀደሰ ባሕል የሚፃረርና የሴቶችን ሥነ-ልቦና የሚሰብር ኢ-ሰብአዊ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በዝርዝር እንዳብራሩት ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ፀጋ ጠብቆ መኖር አለበት ሲባል ከእግዚአብሔር ፈቃድና ትዕዛዝ ውጭ በራሱ ጥበብና አመለካከት የሚፈፅመው ተግባር ሁሉ የማያዋጣ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ድርጊቱን በተግባር ከመፈፀሙ በፊት ማሰብ፣ መመራመርና መረዳት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ይህን በምክንያት አስደግፈው እንደገለፁት የተሳሳተውን ለማረምና ለማስተካከል፣ መሰናክሉን ለማደላደል፣ የከበደውን ለማቅለል፣ ለረዥም ጉዞ የሚደረገውን መንገድ በአጭር እርምጃ ለማጠቃለል አመች ሁኔታ እንዲፈጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛትን እና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የሃይማኖት አባቶች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የአንስታይ ፆታ ግርዛት አላስፈላጊና ጎጂ መሆኑን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መግለጽ እንዳለባቸው ብፁዕ ሳሙኤል አሳስበዋል፡፡ ወላጅ እናቶችና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድርጊቱን በመኮነን ችግሩን ማስወገድ እንደሚገባም በአባትነት ምክራቸው አደራ ብለዋል፡፡

ድርጊቱን ከመግታት ጋር ተያይዞ በከተማም ሆነ በገጠር፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ካህናትና ምዕመናን ቆርጠው መነሳት መቻላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊና የተፈጥሮ ሕግን ማክበር ከመሆኑም በላይ የሴቶችን ሕይወት ለመጠበቅ አማራጭም፣ ተለዋጭም ሂደት የሌለው መሆኑን ያመለከቱት ብፁዕነታቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ሊያወግዘውና በማንም ላይ እንዳይፈጽመው ግንዛቤ መፈጠሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በኢ.ኦ.ተ.ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው ረዴ በበኩላቸው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ መዋቅር እስከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ መድረስ የሚችል በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ አቅሙ እንዳላት ገልፀዋል፡፡ በልማት ኮሚሽኑ አማካኝነት እስከዛሬ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ማሳያ ሊሆኑ እንደሚችሉም አውስተዋል፡፡

ልማት ኮሚሽኑ ልማትን ከማስፋፋትና ሴቶችን የልማት ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገበ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነሩ በሥነ-ፆታ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችንና የሴት ልጅ ግርዛትን ከመቅረፍ አኳያም የላቀ ሚና መጫወት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡ የልማት ኮሚሽኑ ባለው የ4ዐ ዓመታት የሥራ ልምድ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥ ዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሴት ልጅ ግርዛትን ማስቀረት የሚችል አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

ልማት ኮሚሽኑ የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ  ትምህርቱ እንዲስፋፋ “የትዕማር ዘመቻ በፆታዊ ጥቃት ላይ” የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሞ ማሰራጨት መቻሉ ካህናት አባቶች የችግሩን አስከፊነት ተረድተው ለእያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በማድረግ ችግሩን ለማስወገድ ዐብይ ምክንያት እንደሚሆን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን የእርዳታ ድርጅት በኢትዮጵያ ተወካይ የነበሩት ሚስተር ሐንስ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት መጽሐፉ ታትሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ጋር ተጣጥሞ መቅረቡ ተቀባይነቱን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት የረዥም ጊዜ ጠባሳን ከማስከተሉም በላይ የመብት ጥሰት መሆኑን የገለፁት ተወካዩ የሃይማኖት አባቶች ችግሩን ለመቅረፍ ቆርጠው መነሳታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም ችግሩ ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ እየተቀነሰ  መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱን ሲጠቅሱ “የቅርብ ለቅርብ ግንኙነቶችና ውይይቶች በግለሰብም፣ በቡድንም ደረጃ መካሄድ መቻላቸው ነው” ብለዋል፡፡  ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች አጥብቆ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የድርጊቱ ተፈጻሚነት በየትም አካባቢ እንዳይሆንና መጠኑም ዜሮ እንዲሆን ቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አባቶች ድርሻቸው የላቀ መሆኑን የገለፁት ሚስተር ሐንስ ቤተ ክርስቲያኗ ሰፊ ምዕመናንን ስለያዘች የልማት ኮሚሽኑ ጠንክሮ መሥራት ችግሩን በቀላሉው ለመቅረፍ እንደሚያስችል አስምረውበታል፡፡ 

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org