የማይሞተው ሞተ - ጌታችን የተናገረው የቅ/ዲዮስቆስ ቅዳሴ - ገጽ ፪፻፬፮ አንቀጽ ፴፭

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ባሕርይ አባቱ ሊአቀርበን ኃጢአት ሳይኖርበት ለእኛ ለአመፀኞች ሰዎች  በኃጢአታችን ምክንያት የማይሞተው አምላክ ሞተ።

እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሞትም በመለኮቱ ግን ሕያው ነው (፩ኛ ዼጥ ፫፥፲፫)

የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንና ኃጢአታችንን ተሸከመ፤ ስለ መተላለፋችን ሕጉንና ትእዛዙን በማፍረሳችን ስለ እኛ ቆሰለ፤ ስለ በደላችን ደቀቀ፤ ማለትም ሥጋውን ቆረሰ ደሙን አፈሰሰ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሲኦል ወደገነት፣ ከውርደትና ከኃሳር ወደክብር ተመለስን። የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሁላችንን ዕዳ፣ ፍዳ በደል በእርሱ ላይ አኖረ (ኢሳ ፶፫፥፬-፭)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ ስቃይ ሳይኖርበት እኛን ከሥቃይ ለማዳን ሲል በለበሰው ሥጋ ተጨነቀ፣ተሠቃየ፣ለመታረድ እንደ ሚነዳ በግ (ጠቦት) በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል ይህ ሁሉ መከራ በእርሱ ይፈጸም ስቃዩ በዛብኝ መከራው ፀናብኝ ብሎ አልተናገረም፣ (አፉን አልከፈተም)ይልቁንም ስለሕዝቡ ኃጢአት ተገርፎ ተሰቅሎ ነፍሱን ከሥጋው ለየ። ይህን ከባድ ስቃይና መከራ ሲፈፅሙበት በሰውነቱ ስህተት በአንደበቱ ሀሰትና ተንኮል አልተገኘበትም። (ኢሳ ፶፫፥፯-፱) ይህን መከራ ሲቀበል በሰውነቱ ስህተት በአንደበቱ ሀሰት ያልተገኘበት አምላክ ከመከራ ከፈተና ያድነን ዘንድ በጎ ፈቃዱ ይሁንልን።

ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ (ቆላ ፪፥፲፫)

አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ቀርባችኋል(ኤፌ፪፥፲፫) በአባታችን በአዳም በደል አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን የሰውና እግዚአብሔር ግንኙነት ተቋርጦ ስለነበረ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ሰውና እግዚአብሔር መታረቁን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተማረ ሐዋርያው ያስተማረው ይህም ብቻ አይደለም።

እርሱ ሰለማችን ነውና ሁለቱን ያዋሐደ የጥልንም ግርግዳ በሥጋው ያፈረሰ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ ሁለቱንም በእርሱ አንድ ያደረገ ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፦ ቀርበው ለነበሩት ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፣(ኤፌ ፪፥፲፬-፲፰)

እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጌዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፣ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፣ በእኛ ላይም የተጻፈውን የእዳ ደብዳቤ ደመሰሰው፣ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።(ቆላ፪ ፲፫፥፲፭)

ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ተጠማ በቸርነቱ የሚያጠጣ የደከመውን የሚያበረታ ስለሰው ልጅ ብሎ ተጠማሁ አለ በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር በሰፍነግ ሞልተው ወደአፉ አቀረቡለት ኢየሱስም ከርቤ የተቀላቀለበት ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ አለ። ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ (ዮሐ ፲፱፥፳፰-፴፩)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸው ሰባቱ (አጽርሐመስቀል) ቃላቶች

 • ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ ይህም አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ ማለት ነው።(ማቴ ፳፯፥፴፩)

 • አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው (ሉቃ ፳፫፥፴፬)

 • እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ (ሉቃ ፳፫፥፵፫)

 • አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ (ሉቃ ፳፫፥፴፮)

 • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ አላት ደቀመዝሙሩንም እነሆ እናትህ አለው (ዮሐ፲፱፥፳፯)

 • ተጠማሁ (ዮሐ ፲፱፥፳፱)

 • ተፈፀመ አለ፣ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ (ዮሐ፲፱፥፴)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ በሰማይ በምድር የተፈፀሙ ሰባት ታምራቶች

በሰማይ የተፈጸሙ ሦስት ታምራቶች፡

 • ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ፀሐይ ጨለመ (ሉቃ ፳፫፥፵፬)

 • ጨረቃ ደም ሆነ፣

 • ከዋክብት ረገፉ፣

በምድር የተፈጸሙ አራት ታምራቶች

 • የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከሁለተ ተቀደደ

 • ዓለቶችም ተሰነጠቁ

 • መቃብሮችም ተከፈቱ

 • ሞተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሰዎች ተነሡ (ማቴ ፳፯፥፶፩-፶፬)

ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋራ በልጁ ታርቅን (ሮሜ ፭፥፲)

እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ አክብሮ በመልኩ ከፈጠረው በኋላ ሕግ ሠራለት ሰውም የተሰራለትን ሕግ አፈረሰ በዚህ ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ጥላቻዎች ተመሰረቱ፣ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ሲኖር ይቅር ባይና ቸር አምላክ የሰውን ንሰሐ ተቀብሎ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጁን ወደዚህ ዓለም ላከው(ዮሐ፲፯፥፰)ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት  ድኀረ ዓለም ከእመቤታች ያለአባት ተወለደ በመወለዱ ጥልን አፈረሰ እርቅን መሠረተ፡

 • በሰውና በእግዚአብሔር መካካል እርቅ ተመሠረተ (ዮሐ፩፥፲፬)

 • የሰውና የመላእክት እርቅ ተመሠረተ(ሉቃ፪፥፰)

 • የህዝብና አህዛብ (መገረዝና አለመገረዝን)እርቅ ተመሰረተ(፩ኛ ቆሮ ፯፥፯፣ሮሜ ፰፥፮)

 • ሕይወትን ሰጠ፤ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍስና ስጋን ለያይቶ ሥጋን በመቃብር አበስብሶ ነፍስን በሲኦል ተቆራኝቶ ለማኖር አስቦ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶ ግን እነዚህን አንድ አድርጎ በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር ፈቀደ (፩ኛተሰ ፬፥፲፬)

ስለዚህ እግዚአብሔር ተበድሎ የበደለውን የሰው ልጅ ጥል በልጁ ደም ከታረቀን እኛም የበደልናቸውን ብቻ ሳይሆን እንደፈጣሪያችን የበደሉንንም ይቅርታ ጠይቀን የመስቀሉ በረከት ተሣታፊዎች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን።

እኛስ ምን እናድርግ

እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና(ዮሐ ፫፥፲፮-፲፯) እንዲሁ ለወደደን ፍጹም ፍቅሩን የማይዘነጋ ውለታውን እያየንና እያስታወስን ሁልጌዜ በበጎ ምግባር በጸና ሃይማኖትና ፍቅር ልንከተለው ይገባል።

እስከሞት ለወደደን አምላክ የምንከፍለው ምንም ዓይነት ክፍያ ባይኖረንም ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ከእኛ የሚጠበቅ ቁም ነገር አለ ይኸውም፡

 • ለአዳም የሰጠውን የድኀነት ቀጠሮ ከሰዓቱ ከዕለቱም አንዲት ሰከንድ ሳይጨምር በሰጠው ቃልኪዳን መሠረት የማዳን ሥራውን በሚገባ እንደፈጸመልን ማወቅ መረዳት፣

 • በሕይወትና በፍቅሩ ከእርሱ ጋር ለመኖር የሕይወት መንገድን መምረጥ፣ እርሱ ራሱ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ››(ዮሐ፲፬፥፮)ብሎ አልና

 • ኑሮአችን በእርሱ እንዲሆን

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለእኛ ሲናገር ‹‹የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል አንዱ ስለሁሉ ሞተ እንግዲያስ ሁሉም ሞቱ›› በሕይወትም ያሉት ለእነርሱ ለሞተ ወዮና ለተነሣው እንጂ ወደፊት ለራሳቸው እንደይኖሩ ስለሁሉ ሞተ ››(ቆሮ ፭፥፲፬)

በዚህ መንገድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኀጢአት የጐሰቆለውን የሰው ልጅ ጠባይ ፈወሰ። ቅዱስ አትናቴዎስ እንደገለጸው የኀጢአት መሰናክልን አስወገደ፤ ከኀጢአት በስተቀር “የእኛ የሆነውን ወስዶ የእርሱ የሆነውን ሰጠን።” በሌላ አነጋገር ኀጢአታችን ተቀብሎ በቅድስናው አነጻን። ያለ ኀጢአት ሥጋችንን ነሥቶ የመለኮቱ ተሳታፊዎች አደረገን።

ጌታችን በመስቀል ላይ ዕዳ በደላችንን አስወግዶ የከፈለውን ሰላምም ሆነ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መድረሳችን ለፍጹም ድኀነታችን ማረጋገጫ ነው። ከእኛ የሚጠበቀው ዋናው ቁም ነገር ደግሞ ስለ በደላችን ክሶ የሞትን ፍርድ ማጥፋትና አእምሮአችንንና ልቦናችንን አድሶ በዕውቀት አብርቶ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እንድንደርስ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በኀጢአት የረከሰውን ጠባያችንን በንሰሐ አስወግደን ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረንን ዘለዓለማዊ ተዋሕዶ እንዲጸና ማድረግም ጭምር ነው። እግዚአብሔርን ወደ መምሰል የሚያስደርሰን ይህ ውሕደት (ተዋሕዶ) ነው።

እግዚአብሔር በኀጢአት የረከሰውን ጠባያችንን ሳያድስና ሳያነጻ ላለፈው ክፉ ሥራችን (ኀጢአታችን) ይቅር ይበለን።

 • “እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ….” ዮሐ ፲፯፥፳፫

 • “….. ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር…..።” ኤፌ ፫፥፲፯

 • “ እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም” ሮሜ ፰፥፩

  • አቤቱ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ! ካንተ ጋር የምንኖር እንዴት ደስተኞች ነን!

  • በዚህ ታላቅ ክብር ያሉ የእግዚአብሔር ልጆች ምንኛ ደስተኞች ናቸው!

  • ዐብሮን የሚኖር ክብርህ፣

  • ከአንተ ጋር ያለን የተዋሕዶ ክብር፣

  • የመለኮታዊ ክብርህ ተሳታፊነታችን፣ደስታችንን ዕጥፍ ድርብ ያደርገዋል። ይህን የተናገርህ አንት ነህ። “ የሚያምንብኝ ቢሞትም እንኳን ሕያው ይሆናል።” ዮሐ ፲፩፥፳፭

  • ስለዚህ አንተን በመጥራት እንከተልሀለን። “በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሽናፊዎች እንበልጣለን።” ሮሜ ፰፥፴፯

  • “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ። እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም። ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል።” ገላ ፪፥፳

ወልድ በተረገመ ዕንጨት ኀፍረታችንን ተሸክሞ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን አደረገ። ሮሜ ፭፥፩ ኤፌ ፪፥፲፫‐፲፮።

በመስቀል ላይ በተደረገው የማዳን ሥራ ውስጥ መለኮትና ትስብእት በተዋሕዶ ባይገለጥ ኖሮ የተደረገው የድኀነት ሥራ ከንቱ ይሆን ነበር። ለድኀነት የመለኮትና የትስብእት ድረሻ በተዋሕዶ ምስጢር ብቸኛ ነው። ዓለምን ለማዳን ከኀጢአተኞች ጋር ተሰቀለ። ኢሳ ፶፫፥ ማቴ ፳፯፥፴፰።

በአለ ዘመናችን በደላችንና ኃጢአታችን ትዝ እያለን ንስሐ በመግባት የጌታን ቅዱስ ሥጋውን በመቀበል ክቡር ደሙን በመጠጣት ከእርሱ ጋር ለመኖር ተጠርተናል እርሱ ‹‹ ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ›› (ዮሐ ፮፥፭)

ስለዚህ በከበረ ደሙ የገዛን እኛ ሁላችን ‹‹ጌታን በመከራው ከመሰልነው በክብር እንመስለዋለን በሞቱም ከመሰልነው በትንሣኤው እንመስለዋለን ››(ሮሜ ፮፥፭) በሞቱ መስለነው በትንሣኤው እንድንመስልው የእግዚአብሔር ረድኤት አይለየን አሜን!!!

"ወስብሐት ለእግዚአብሔር"

ብፁዕ አቡነ ሣሙኤል

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፣

የኪራይ ቤቶች  አስተዳደርና ልማት ድርጅት የበላይ ሃላፊ

አዲስ አበባ

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org