በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ሀልዎተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መኖር)

አንቀጽ 1 እግዚአብሔር የሚለው ስም የባሕርይ ስም ነው፡

ትርጉሙም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ ማለት ነው፡፡ የማይታይና የማይመረመር ሁሉን ማድረግ የሚችል ሁሉንም የፈጠረ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘለዓለማዊ አምላክ መኖሩና ራሱን ለሰው ልጆች እንደገለጠ በቅዱሳት መጻሕፍት ተረጋግጧል፡፡ (ዘጸአ 3¸6)   የዚህን ዘለዓለማዊ አምላክ መኖር ከሚያስረዱን የአእምሮ ማስረጃዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ፍጥረት፡- የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መኖር ለመረዳት ብዙ ተመራምሯል፡፡ በምርምሩም የእግዚአብሔርን መኖር ወደማወቅ የሚያደርሱ መንገዶችን አግኝቷል፡፡ ለማንኛውም ነገር ምክንያት አለው፡፡ ለሥዕል ሠዓሊ፣ለመጽሐፍ ጸሐፊ፣ ለወንበር ጠራቢ አለው፡፡ ለሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ አንቀሳቃሽ አለው፡፡ በዚህ መሠረት “ፍጥረት ለፈጣሪ የተገኘ አይደለም” ወደሚለው እምነት ተደርሷል፡፡ ፍጥረት ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ፣ አእምሮ ከሌለው ጀምሮ ከፍተኛ አእምሮ እስካለው ድረስ የእግዚአብሔርን መኖር ወደማወቅ ይመራል፣ ስለዚህም ሰሎሞን “እግዚአብሔርን የማወቅ ጉድለት በልባቸው ያለባቸው ሰዎች ሁሉ በእውነት ከንቱ ናቸውና በእነዚህ በሚታዩ ፍጥረቶቹ በዚህ ዓለም የሚኖር እርሱን ያውቁ ዘንድ ተሳናቸው፣ ሥራውን እያዩ ፈጣሪያቸውን አላወቁም፣…….. ፀሐይና ጨረቃን አይተው የፈጠራቸውን ይወቁ……” (ጥበብ 13¸1-10) ይላል፡፡ ኢዮብም “እንሰሶችን ጠይቅ ያስተምሩህማል፣ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ ይነግሩህማል፣ ወይም ለምድር ተናገር እርስዋም ታስተምርሀለች፣ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል፣ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደርግ፣ ከእነዚህ ሁሉ ይህን የማያውቅ ማን ነው?” ብሏል (እዮብ 12¸7-9)፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር 18¸1-2 “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይ ጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያወራል” በማለት ተናግሯል፡፡

 

ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ለፍጥረቱ እንደሚታወቅ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡፡ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በሥነ ፍጥረት ይታወቃል፡፡” (ሮሜ 1¸9-20)፡፡ ልቡና፡- “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና” (ሮሜ 2¸14-15) ታሪክ፡- በዚህ ዓለም አምልኮት የሌለው ሕዝብ እንዳልኖረ የሰው ልጅ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስከ አለንበት ዘመን ድረስ የአምልኮቱ ዓይነት ይለያይ እንጂ ሁሉም በየወገኑ ባዕድ አምላክ ወይም ብዙዎች አማልክትን ያመልካል፡፡ ይህም ሁሉ የሚያሳየው የአንድ እውነተኛ አምላክ መኖርን ነው፡፡ እግዚአብሔር ባይኖር ሰው ይህን የአምልኮት ጠባይ ከየት ሊያገኝ ቻለ? (የሐዋ 14¸11-16፣ 17¸26-29)፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር መኖር በሰፊው ከመነገሩም በላይ ስለ እርሱ የተሰጡ መግለጫዎች አሉ፡፡ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡ ቅድስና፡- እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፡፡ ከክፉ ወይም ከርኩስ ነገር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ እርሱ ራሱ “እኔ ቅዱስ እንደሆንሁ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ”ሲል ተናግሯል፡፡ (ዘሌዋ 19¸2፡፡ 1ጴጥ 1¸16)፡፡ ሁልጊዜ በመላእክት ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ እየተባለ ሲመሰገን ይኖራል፡፡ (ኢሳ 6¸3)፡፡

ፍቅር፡- እግዚአብሔር ፍቅር በመሆኑ ፍጥረቱን ይወዳል መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ለፍጥረቱ ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑ በወንጌላዊው ዮሐንስ ወንጌልና መልእክታት ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ (1ዮሐ 4¸8) በኋላም ሰው መሆኑ ፍቅሩን ያመለክታል፡፡ (ዮሐ 3¸16፡፡ ሮሜ 5¸5)፡፡ ጽድቅ፡-እግዚአብሔር በሁሉ እውነተኛ ነው፡፡ በእውነተኛነቱ ለሁሉ በትክክል ይፈርዳል፡ (1ሳሙ 2¸2¸2 ጢሞ 4¸8) ዮሐንስ በራእዩ 16¸7 “አዎ ጌታዬ ሁሉን የምትገዛ ፍርድህ እውነተኛና የሚገባ ነው” ይላል፡፡ ጥበብ፡- ፍጥረትን የፍጥረቱን ሥነ ሥርዓት ክንውን ስንመለከት የእግዚአብሔርን ፍጹም ጥበብ እንረዳለን፡፡ ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔር በጥበብ የሠራውን ሁሉ በማድነቅ እንዲህ ይላል፡፡ “አቤቱ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው ሁሉን በጥበብ አደረግህ” (መዝ 103¸24)፡፡ ከአንድ እስከ አራት ከተመለከትናቸው የባሕርዩ መግለጫዎች የተለዩ ሌሎች የእግዚአብሔር የባሕርዩ መግለጫዎች አሉ፡፡ ሁሉን ቻይነት፡- (ከሃሌ ኩሉ)፡- ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ፈጽሞ የለም ሁሉን ማድረግ ይችላል እግዚአብሔር ራሱ ለአብርሃም “ሁሉን ቻይ ነኝ” ብሎ ገልጦለታል፡፡ (ዘፍ 17¸1፡፡ 18¸14፡፡ ሉቃ 1¸37) ሁሉን ማወቅ፡- እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ከመሆኑ በፊት ያውቀዋል፡፡ ነገሮችን ሁሉ ከመታሰባቸውና ከመሠረታቸው በፊት ያውቃቸዋል፡፡ (መዝ 138¸2፣ ዮሐ 2¸25)፡፡ ምሉዕነት፡-    እግዚአብሔር በቦታና በጊዜ አይወሰንም በየትም ቦታ አለ ምንም እንኳን ስለ ልዕልናው በሰማይ እንደሚኖር ቢነገርም በሰማይ ብቻ አይወሰንም፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይላል “ከመንፈስ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ ወደ ሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ…..” (መዝ 138¸7-10፡፡ ኤር 23¸23 ሠለስቱ ምእት ቅዳሴ) ዘለዓለማዊነት፡- እግዚአብሔር በዘመናት አይወሰንም ከዘመን በፊት ነበረ ዘመናትንም አሳልፎ ይኖራል፡፡ (መዝ 89¸1-2) በጠቅላላ አነጋገር እግዚአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም ራሱ መጀመሪያና መጨረሻ ነው በእርሱ ዘንድ ለውጥ የለም፡፡ (ኢሳ 44¸6፡፡ ያዕ 1¸17)

አንቀጽ 2 ሥነ - ፍጥረት ቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔርን መኖር በማረጋገጥ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ በማለት ይጀምራል፡፡(ዘፍ 1¸1) ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ 3¸4 ላይ “ሁሉን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው” ይላል፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን አስገኘ ለሁሉ ነገር መገኛ ጥንትና መሰረት ነው፡፡ ለእርሱ ግን ለህላዌው ምክንያት የለውም፡፡ (የሐዋርያት ጸሎት ሃይማኖት) እግዚአብሔር ይህን የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም በውስጣቸውም ያሉትን ሁሉ ከቸርነቱ ብዛት የተነሣ ፈጠረ፡፡ (ኢሳ 42¸5)፡፡ እግዚአብሔር ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ያስገኘው “ለይኩን” ባለው ቃሉ ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ምንም ነገር አልነበረምና (ጥበበ ሰሎሞን 11¸17፡፡ 1መቃብ 27¸1 ቅዱስ ጳውሎስም “ዓለሞች ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠሩ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን” (ዕብ 11¸3) በማለት እግዚአብሔር ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ መፍጠሩን አስረድቷል፡፡ ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን በየመልኩና በየወገኑ መፍጠሩ ክብሩ ይገለጥበትና ስሙ ይቀደስበት ዘንድ ነው፡፡ ይህንም ነቢዩ ኢሳይያስ “ፍጥረታትን ሁሉ ለክብሬ ፈጠርኋቸው አለ እግዚአብሔር” ብሎ ተናግሯል፡፡

(ኢሳ 43¸7) ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው ከዕለተ እሑድ እስከ ዕለተ ዓርብ ባሉት ስድስት ቀናት በቅደም ተከተል መፈጠራቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ እነዚህም በስድስቱ ዕለታት የተፈጠሩ ፍጥረታት በየወገን በየወገናቸው ተቆጥረው ሃያ ሁለት መሆናቸውን መጽሐፈ ኩፋሌ ይናገራል፡፡(ዘፍ 1¸1-31) ኩፋሌ 3¸9) እነዚህን ሁሉ ፍጥረታት በየወገኑ ከፈጠራቸው በኋላ መልካም እንደሆኑ አይቶ እግዚአብሔር በሥራው ደስ አለው እንዲበዙም ባረካቸው፡፡ (ዘፍ 1¸21፡1፣መዝ103¸ 31)፡፡ ሀ/ የሰው ተፈጥሮ እግዚአብሔር ከዕለተ እሑድ እስከ ዕለተ ዐርብ ያሉ ፍጥረታትን በየዓይነታቸው ከፈጠረ በኋላ ሰውን የእነዚህ ሁሉ የበላይ ገዢ አድርጐ በመልኩና በአርአያው ፈጠረው በደመ ነፍስ ሕይወት ከሚኖሩ ፍጥረታት የምትለየውን ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት ነፍስን በውስጡ አሳደረበት፡፡ ወንድና ሴትም አደረጋቸው “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ግዙአትም” ብሎ ባረካቸው፡፡ ዘፍ 1¸26-28)፡፡ በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተፈጠረው ሰው ባለ አእምሮ ፍጡር ነው፡፡ 7ኛ ቀን፡- “እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ከመፍጠር ሥራ ዐረፈ፡፡ ስለዚህም ሰባተኛይቱን ቀን የዕረፍት ቀን እንድትሆን ባረካት ቀደሳትም” ተብሎ ተጻፈ፡፡ (ዘፍ 2¸3) ስለዚህ እግዚአብሔር የፍጥረታት ሁሉ አስገኝና ባለቤት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን በሥልጣኑ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን መጋቢው መሪውና ጠባቂውም ነው፡፡ (መዝ 103¸27-31፡፡ 1ቆሮ 3¸22፡፡ 15¸28፡፡ የሐዋ 14¸17)፡፡

አንቀጽ 3 አምስቱ አዕማደ ምሥጢር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሠረተ እምነትዋን የምትገልጥባቸውና የምታስተምርባቸው አምስት አዕማደ ምሥጢር አሏት፡፡ አዕማድ ማለትም ምሰሶዎች ማለት ነው፡፡ የምሥጢር ምሰሶዎችም የተባሉበት ምክንያት ቤት በምሰሶ ተደግፎ እንደሚጸና ምእመናንን በትምህርተ ሃይማኖት ደግፈው የሚያጸኑ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህም አምስቱ አዕማደ ምሥጢር መጽሐፋዊ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ (1ቆሮ 14¸19)፡፡ 1. ምሥጢረ ሥላሴ ይህ ክፍል የሥላሴ አንድነትና ሶሦትነት የሚገለጥበት የምሥጢር ዓምድ ነው፡፡ ሥላሴ በስም በግብር፣ በአካል ሶስት ሲሆኑ በባሕርይ፣ በመለኮት፣ በህልውና በፈቃድ አንድ ናቸው፡፡ የስም ሶስትነት፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ የግብር ሶስትነት፡ አብ ወላዲ፣ ወለድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ነው፡፡ የአካል ሶስትነት፡     ለአብ ፍጹም አካል አለው፣ ለወልድ ፍጹም አካል አለው፣ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል አለው፡፡ አብ ልብ ነው፡፡ ወልድ ቃል ነው፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ነው፡፡ ወልድ ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለራሱ እስትንፋስ (ሕይወት) ሆኖ ለአብና ለወልድ እስትንፋስ (ሕይወት ) ነው፡፡ ሥላሴ በስም፣ በግብር፣ በአካል ሶስት ናቸው ብንልም በባሕርይ በመለኮት በህልውና በፈቃድ አንድ ስለሆኑ አንድ አምላክ እንጂ ሶስት አማልክት አይባሉም፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በየአካላቸው ሲኖሩ ህልውናቸው አንዲት ናት፡፡ (አቡ ሊዲስ ሃይ.አ/ምዕ 40 ክፍ 4 ቁ 6፡፡) የሥላሴ የሶሦትነት ስማቸው የአንዱ ወደ አንዱ አይፋለስም፡፡ ይህም ማለት የአብ ስም ተለውጦ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የወልድ ስም ተለውጦ አብ መንፈስ ቅዱስ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስም ተለውጦ አብ ወልድ ተብሎ አይጠራም፡፡ አብ አብ ነው፣ ወልድ ወልድ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ሶስቱም በየስማቸውና በየአካላቸው ጸንተው ይኖራሉ (አግናጢዎስ ሰማዕት ሃይ. አበ)ምዕ 11 ክፍ 1 ቁ 7-8፡፡) በአንድነት ስማቸው ግን፡- እግዚአብሔር አምላክ በመባል ሶሦቱም ይጠሩበታል፡፡ እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር፡፡ አብ አምላክ ወልድ አምላክ መንፈስ ቅዱስ አምላክ አንድ አምላክ ይባላል፡፡ ይህንም ሶሦት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንት በሃይማኖት አበው ሲያስረዱ “በእግዚአብሔር አብ በእግዚአብሔር ወልድ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እናምናለን” ብለዋል” (ሃይ አበ ዘሠለስቱ ምእት/ምዕ 19 ክፍል 1 ቁጥር 30፡፡) የእስክንደርያው ሊቀ ጳጳሳት ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስም “አብ አምላክ ነው ወልድ አምላክ ነው መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ግን አንድ አምላክ እንጂ ሶስት አምላክ አይባሉም” በማለት ገልጿል፡ (ሐዊርያዊ አትናቴዎስ ሃይ.አቡ፡፡ ምዕ 24 ክፍ 4 ቁጥር 4) ስለ ሥላሴ አንድነትና ሶስትነት በብሉይና በሐዲስ ኪዳናት በብዙ ቦታ ተገልጿል፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘፍ 1¸26፣ 2¸18፡፡ 3¸22፡ 11¸7፡፡ 18¸1-3፡፡ መዝ 33¸6፡፡ 146¸5፡፡ ኢሳ 6¸3፣8፡፡ በሐዲስ ኪዳን ማቴ 3¸16-17፡፡ 28¸19፡፡ ዮሐ 14¸26፡፡ 2ቆሮ 14¸13፡፡ 1ጴጥ 1¸2፡፡ ዮሐ 5¸7-8፡፡ 2. ሚስጢረ ሥጋዊ ምሥጢረ ሥጋዊ ከሶሦቱ አካላት አንዱ፡- እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋም ነፍስ ነስቶ በሥጋ የመገለጹ አምላክ ሰው ሰው አምላክ የመሆኑ ምሥጢር ነው፡፡ “ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” (ዮሐ 1¸14) እግዚአብሔር ወልድ ሰው የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አዳምንና ሔዋንን በንጹሕ ባሕርይ ያለሞት ፈጥሯቸዋል፡፡ “እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና”፡፡ (መጽ ጥበብ 1¸13)፡፡ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የተሰጠውን ትእዛዝ በማፍረስ ስለ በደለ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ርደተ መቃብርና ርደተ ገሃነም ተፈረደበት (ዘፍ 3¸19-24 እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረትን ፈጥሯል እንጂ የሰዎች ጥፋት ደስ አያሰኘውም በእጃችሁ ሥራ  ሞትን አታምጡ፡፡ የሰውም መፈጠር ለደኅንነት ነውና፡፡ ሕይወት የማታልፍ ስለሆነች ለመቃብርም በዚህ ዓለም ግዛት አልነበረውምና እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች ግን በቃል ጠሩት፡፡ ባልንጀራም አደረጉት በዚሁም ጠñ (ሮሜ 5¸12-14) ይህ ሁሉ መከራ የመጣባቸው ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፋቸው መሆኑን አውቀው ተጸጸቱ አዘኑ አለቀሱ ንስሓ ገብተው ፈጣሪያቸውን ለመኑት፡፡

እግዚአብሔርም በፈታሒነቱ አንጻር መሐሪነቱ አለና የአዳምንና የሔዋንን ንስሓቸውን ተቀብሎ ኀዘናቸውንና ለቅሶአቸውን ተመልክቶ ሊያድናቸው ወደደ ተስፋም ሰጣቸው (ኢሳ 63¸8፣ ዕብ 2¸14-16፡፡) ይህም የተሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበት ዘመን በደረሰ ጊዜ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ ልዑል እግዚአብሔር ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድ የባሕርይ ልጁን ወደ ዓለም ላከው እግዚአብሔር ወልድም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡ ሰው ሆነ ማለትም በተለየ አካሉ ነፍስና ሥጋን ተዋሐደ ማለት ነው፡፡ በዚህም የነቢያት ቃል ሁሉ ተፈጸመ (ኢሳ 7¸14፣ 9¸6 ሚክ 5¸2፣ ገላ 4¸4)፡፡ መለኮት ከሥጋ ሥጋ ከመለኮት ጋር ያለ መለወጥ ያለመቀላቀል ያለ መለያየትና ያለ መከፈል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ፡፡ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ሰውም ከሆነ በኋላ አንድ ወልድ አንድ ክርስቶስ ነው፡፡ (ቄርሎስ ሃይ. አበ. ምዕ. 78 ክፍ 48 ቁ 9-18)፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም፡- “በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ አምላክም የሆነ ሰው እርሱ ብቻ ነው” ብሏል፡፡(ዮሐ አፈ. አይ/አ/ምዕ 66. ክፍ 9 ቁጥ 18-19)፡፡ ከተወለደም በኋላ ከኃጢአት በቀር ሰው የሚሠራውን ሥራ ሁሉ እየሠራ አደገ በዚህም ዓለም 33 ዓመት ከሶስት ወር ኑሮና አስተምሮ ስለእኛ የሞት ፍርድን ተቀበለ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፤ በሞቱም ሞትን አጠፋ ዓለምን አዳነ ሶስት መዓልት ሶስት ለሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ፡፡ ከተነሣም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እየታየ ጉባኤ ሠርቶም መጽሐፈ ኪዳንን እያስተማረ በምድር ላይ አርባ ቀን ቆየ፡፡ በአርባኛውም ቀን ደቀ መዛሙርቱ እያዩት በመላእክት ምስጋናና በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ (ዕሪና) ተቀመጠ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድና ለሁሉም እንደሥራው ዋጋውን ይከፍል ዘንድ ይመጣል፡፡ (ዮሐ 3¸13፡፡ 1ጴጥ 3¸22፡፡ ማቴ 25¸31፡፡ ኤፊ 4¸8-10፡፡ የሐዋ 2 30፡፡ 2ቆሮ 5¸14፡፡)

ስለዚህ በምሥጢረ ሥጋዌ የሚገለጠው ትምህርት ክርስቶስን ቃለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ ድንግል ማርያምን በአማን ወላዲተ አምላክ ወላዲተ ቃል ብሎ ማመን ነው፡፡ ቄርሎስ ሃያ/አ)፡፡ 3. ምሥጢረ ጥምቀት፣ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ ለሚያምን ሰው ሁሉ የሚሰጥ የኃጢአት መደምሰሻ ከእግዚአብሔር የልጅነትን ጸጋ መቀበያ የመንግሥተ ሰማያትም መውረሻ ነው፡፡ ምሥጢር መባሉም ካህኑ ለጥምቀት የተመደበውን ጸሎት አድርሶ ሲባርከው ውሃው ተለውጦ ማየ ገቦ ስለሚሆንና ከእግዚአብሔር ዘንድ የጸጋ ልጅነትን ስለሚያሰጥ ነው፡፡ (ዮሐ 19¸34-35)፡፡ አምኖ የሚጠመቅ ሁሉ የኃጢአት ሥርየትን ያገኛል፣ “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት፡- ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” (ጸሎተ ሃይማኖት) ማንም ሰው በጥምቀት ከእግዚአብሔር ይወለዳል፣ ከፍዳ ይድናል፡፡ “ያመነ የተጠመቀመ ይድናል ያላመነና ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” (ማር 16¸16፣ የሐዋ 2¸28)፡፡ ከሥላሴ መወለድም የእግዚአብሔርን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያትም በጥምቀት እንጂ ያለ ጥምቀት ልንገባበት እንደማንችል ጌታችን አስተምሯል፡፡ “እውነት እውነት እልሀለሁ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት አይችልም” (ዮሐ 3¸5፡፡ ቲቶ 3¸4-7)፡፡ 4. ምሥጢረ ቁርባን ቁርባን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፡፡ ሥጋዬና ደሜ ሕይወትነት ያለው እውነተኛ ምግብ ነውና፡፡ ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ ከእኔ ጋር ይኖራል፡፡ እኔም ከእርሱ ጋር እኖራለሁ” (ዮሐ 6¸53-57)፡፡ ተብሎ ተጽፏል፡፡ 5. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ትንሣኤ ሙታን ማለት ከአዳም እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩና የሚለዩ የሰው ልጆች ሁሉ በነፍስና በሥጋ አዲስ ሕይወት ለብሰው የሚነሡበት ምሥጢር ነው፡፡ ሰው ሁሉ በሚሞትበት ጊዜ የጻድቅም ሆነ የኃጥእ ሥጋው በመቃብር ይቆያል፡፡ የጻድቃን ነፍስ በገነት የኀጥአን ነፍስ በሲኦል ትቆያለች፡፡ (ሉቃ 16¸19-31)፡፡ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በሚመጣበት ጊዜ የሰው ልጆች ሁሉ ይነሣሉ፡፡ “ስለዚህ ነገር አታድንቁ በመቃብር ያሉት ሙታን ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ሰዓት ትመጣለች ሕጉን የፈጸሙ የሕይወት ለመኖር ይነሣሉ፡፡ ክñ ሥራን የሠሩት ግን በፍዳና በጨለማ ለመኖር ይነሣሉ”፡፡ (ዮሐ 5¸28)፡፡ ስለ ትንሣኤ ሙታን እምነትና ትምህርት ማረጋገጫ በብሉያት በሐዲሳት በብዙ ቦታ ይገኛል፡፡ በዘዳግም 32¸39 ላይ “እኔ እገድላለሁ አድንማለሁ” በማለት ራሱ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ተስፋ ትንሣኤን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ “ሙታን ይነሣሉ በመቃብር ያሉ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ በምድር ውስጥ ያሉም ደስ ይላቸዋል፡፡ ከአንተ የሚገኝ ጠል ሕይወታቸው ነውና”፡፡ (ኢሳ 26¸19-20)፡፡ ዳንኤል “በዚያም በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል፡፡ በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎቹ ይነቃሉ እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እኩሌቶቹም ወደ ዕፍረትና ወደ ዘለዓለም ጉስቁልና ይሄዳሉ” በማለት ተናግሯል፡፡ (ዳን 12¸1-3)፡፡ “እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደሆነ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፡፡ እኔ ራሴ አየዋለሁ ዓይኖቼ ይመለከቱታል” ሲል ኢዮብ የትንሣኤን ነገር ገልጧል፡፡ (ኢዮብ 19¸25-27)፡፡ የትንሣኤ ሙታን ትምህርት በቃል ብቻ የተነገረ አይደለም ከሞቱ ሰዎች መካከል እየተነሡ በተግባር ተገልጧል ነቢዩ ኤልያስና ደቀመዝሙሩ ኤልሳዕ ሙታንን አስነሥቷል፡፡ (1 ነገሥ 17¸21፡፡ 2ነገሥ 13¸21)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ዓለም በሚያስተምርበት ጊዜ ሙታንን አስነስቷል፡፡ (ማቴ 9¸25፡፡ ሉቃ 7¸15፡፡ ሉቃ 7¸15፡፡ ዮሐ 11¸14)፡፡ እንደዚሁም ሐዋርያት በትምህርት ጊዜያቸው ሙታንን አስነስተዋል፡፡ ጌታችን በተሰቀለበትም ዕለት ከእግረ መስቀሉ ብዙዎች ሙታን ተነሥተዋል፡፡ (ማቴ 27¸52)፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው የሰው ልጅ በመቃብር ውስጥ ፈርሶና በስብሶ እንደ ማይቀርና በመጨረሻ ቀን እንደሚነሳ ነው፡፡ ለትንሳኤያችን መሠርት የምናደርገው ግን የክርስቶስን ትንሣኤ ነው፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ እኛንም በሐዲስ ትንሣኤ እንደሚያስነሣን እናውቃለን” (2ቆሮ 4¸14)፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት አሞንዮስና አውሳብዮስም “ክርስቶስ የሥጋችንን መነሣት ያስረዳን ዘንድ ተነሣ” ብለዋል፡፡ (መቅድመ ወንጌል) ትንሣኤ ለሰው ዘር ሁሉ ነው፣ ጻድቃንም ኃጥአንም ይነሣሉ፡ የመጨረሻው የሙታን ትንሣኤ የሚሆነውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ በሚመጣበት ጊዜ ነው፡፡ በዘመኑ መጨረሻ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ በክብሩና በጌትነቱ ይመጣል፡፡ (መዝ 49¸2/ማቴ 25¸31-32፡፡ ራእ 1¸7)፡፡ አስቀድሞም መላእክትን ይልካቸዋል፡፡ እነርሱም የመለከት ድምጽ ያሰማሉ ሙታንም ይነሣሉ ምድርም አደራዋን ታስረክባለች፡፡ ከዚህ በኋላ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው ያቆማቸዋል ያን ጊዜ ጻድቃን በበጎ ምግባራቸው ይመሰገናሉ ኃጥአንም በክፉ ምግባራቸው ይወቀሳሉ፡፡ ጻድቃን ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርተው አምላካቸውን ክርስቶስን መስለው መንግሥቱን ይወርሳሉ፡፡ ኃጥአን ግን ጠቁረው ጨለማ ለብሰው ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም ኩነኔ ይሄዳሉ፡፡ (ማቴ 13¸42-49፡፡ ማቴ 25¸31-43፡፡ 2ቆሮ 5¸10፡፡ ራእ 20¸12)፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖትን ለምእመናን የምታስተምረው ከዚህ በላይ በአምስት ተከፍለው በተገለጡት አዕማደ ምሥጢር መሠረትነት ነው፡፡

አንቀጽ 4 ሰባቱ ምሥጢራት ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰባት ዐበይት ምሥጢራት ምእመናንን ታገለግላለች ምሥጢራት የተባሉበትም ምክንያት በዓይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚሁ ምሥጢራት አማካይነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው፡፡ ሰባቱ ምሥጢራት 1ኛ. ጥምቀት 2ኛ. ቅብዓተ ሜሮን          5ኛ. ተክሊል 3ኛ. ቁርባን                6ኛ. ንስሐ 4ኛ ክህነት                 7ኛ. ቀንዲል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአዕማድ ምሳሌነት ለምሳሌ ሰሎሞን የተነገረውን መነሻ በማድረግ ምሥጢራት ሰባት መሆናቸውን ተቀብላ ታስተምራለች ምሳሌ፡ ሰሎሞን 9¸1 እነዚህ ሰባት ምሥጢራት በሚታየውና በሚዳሰሰው በግዙፉ አካል አማካይነት ረቂቁን የማይታየውንና የማይዳሰሰውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ለምእመናን የምታሳትፍባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሰባት ምሥጢራት ስድስቱ በጳጳስም በቄስም ይፈጸማሉ የክህነትን ሥልጣን መስጠት ግን የሚፈጸመው በጳጳስ ብቻ ነው፡፡ 1. ጥምቀት ጥምቀት፡- ከሰባቱ ምሥጢራት የመጀመሪያው ጥምቀት ነው፣ ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንገባበት ምሥጢር ነው፡፡ ዮሐ 3¸5 ጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ አለው፡፡ (ማቴ 28¸19-20)፡፡ በጥምቀት ኃጢአት ይሠረያል የሐዋ ሥራ 2¸8፡፡ መንጻትና መቀደስም በጥምቀት ነው፡፡ (1ኛ ጴጥ 3¸ 21፣ ቲቶ 3¸5-6)፡፡ 2. ሜሮን ሜሮን፡- ተጠማቂው ከማጥመቂያው ሲወጣ የሚቀባው ቅዱስ ዘይት ነው፡፡ ሜሮን እንደ ጥምቀት ነው፡ አይደገምም፡፡ በቅብዐ ሜሮን ተጠማቂው የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ይቀበላል፡፡ በሐዋርያት ጊዜ አማኞች ከተጠመቁ በኋላ በአንብሮተ እድ መንፈስ ቅዱስን ያሳድሩባቸው ነበር፡፡ (የሐዋ ሥራ 20¸14-17)፡፡ ቤተክርስቲያን እየተስፋፋች በሔደች ጊዜ ግን በአንብሮ እድ ፋንታ በሐዋርያት መንበር የተተኩ ኤጴስ ቆጶሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ሜሮን እያዘጋጁ አዲስ የተጠመቀ ሁሉ እንዲታተምበት ፈቀዱ፡፡ 3. ምሥጢረ ቁርባን በቤተክርስቲያናችን የምሥጢራት ሁሉ መደምደሚያ ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡

ቁርባን ማለት መሥዋዕት ማለት ነው፡፡ ይኸውም ሰው--- ዮሐ 6¸54፣ ማቴ 26¸27፣ 1ቆሮ 11¸23 4. ክህነት ክህነት፡- የቤተክርስቲያን ከፍተኛው መንፈሳዊ መዐርግ ነው፡፡ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የተወሰኑ ሰዎችን ለክህነት መርጧል፡፡ ሉቃ 6¸12፣ ማቴ 28¸19¸20፡፡ ኤô 44¸11፡፡ የሐዋ ሥራ 28¸20)፡፡ 5. ተክሊል የክርስቲያኖች ጋብቻ በቤተክርስቲያን ምስክርነት የሚፈጸም ጸጋ መንፈስ ቅዱስንም የሚያሰጥ ስለሆነ ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ ነው፡፡ ጋብቻ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት አለው፡፡ (ዘፍ 1¸27-28፡፡ 2¸18፣ ማቴ 19¸4-6)፡፡ 6. ንስሓ ንስሓ፡- መጸጸት፣ መመለስ፣ ከኃጢአት መንጻት ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች በጥምቀት እንደገና የተወለዱ ቢሆኑም እያንዳንዱ ክርስቲያን መምህረ ንስሓ ሊኖረው ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች ወደ መምህረ ንስሓ እየሄዱ ኃጢአታቸውን ይናዘዛሉ፡፡ (ዘሌ 14¸31፣ ማቴ 8¸4፣ ኤጲፋንዮስ ሃያ አበ ምዕ 59 ቁ. 20)፡፡ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ያደረጉት መከራና ኃጢአታቸውንም መናዘዛቸው ጸጋ እግዚአብሔርን ያሳጣቸዋል፡፡ ሥጋውን ደሙን ተቀብለው ወደ ቀደመ ክብራቸው ይገባሉ፡፡ ማቴ 8¸4-3፣ ዘካ 1¸3 7. ቀንዲል ቀንዲል፡- ቤተክርስቲያናችን ከምትገለገልባቸው ሰባት ምሥጢራት አንዱ ነው፡፡ ይህ ምሥጢረ ቀንዲል ለበሽተኞች የሚቀባ ነው፡፡

አንቀጽ  5 ቅዱሳት መጻሕፍት ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተጻñ ወይም እስተንፋሰ እግዚአብሔር ናቸው፡፡ በሌላም አገላለጽ መጻሕፍት አምላካውያት ይባላሉ፡፡ (ፍት.ነገ.አን.2)፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ለመሆናቸው ወይም በመንፈሰ እግዚአብሔር ለመጻፋቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ጢሞ 3¸14 “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ብሎ ጽፏል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያም “ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ናቸው” ብሏል፡፡ (ቄር.ሃይ/አበ 78¸67)፡፡ በመሆኑም በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈው ሁሉ ፍጹም እውነት ነው፡፡ ሊለወጥ ሊሻሻል ሊጨመርበት ወይም ሊቀነስበት የማይቻል ነው፡፡ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተቃኙ ቅዱሳን ሰዎች ጽፈውታልና (2ጴጥ 1¸20፡፡ ማቴ 5¸18፡፡ ሉቃ 16¸17)፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳት መጻሕፍትን “እንዲህ ብለህ ተናገር እንዲህ ብለህ ጻፍ” እያለ ድምፁን በማሰማት በራእይ እየተገለጸ በልቡና እየቀረፀ እንዲጻፉ ማድረጉ ተገልጧል፡፡

(ዘጸአ 34¸27፡፡ ዘዳግ 31¸19፡፡ ኢሳ 8¸1)፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቀኖና የተቀበለቻቸው የብሉያትና የሐዲሳት መጻሕፍት ቁጥር 81 ነው፡፡ የሥርዓት መጻሕፍት የብሉይ ኪዳን መጽሕፍት ድምር 46 የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ድምር 35 ጠቅላላ ድምር 81 ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የተለያየ አ„ጣጠር ቢኖርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምትቀበላቸውና በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ተዘርዝረው የሚገኙ መጻሕፍት ከዚህ በላይ የተመለከቱ 81 መጻሕፍት ናቸው፡፡ ከነዚህም ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በብሉይና በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ የብሉያትና የሐዲሳትን ምሥጢራት አብራርተውና አጉልተው የሚገልጡ በልዩ ልዩ ቅዱሳን አበው የተደረሱ የሃይማኖት የትምህርት የጸሎት መጻሕፍት ከብሉያትና ሐዲሳት ተውጣጥተው የተደረሱ የቅ/ያሬድ የፀዋትወ ዜማ መጻሕፍት በሙሉ ሌሎችም የአገልግሎት መጻሕፍት አሏት፡፡

አንቀጽ 6 ትውፊት ትውፊት ማለት ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያን በኩል ቃል በቃል ሲነገር የመጣ በቃልም በጽሑፍም ከአበው ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ እምነቱንና ሥርዓቱን ባህሉንና ታሪኩን በጽሑፍ ከመያዙ አስቀድሞ ከአዳም እስከ ሙሴ ቃል በቃል እየተነገረ በተላለፉ ትውፊት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይህ የትውፊት አመጣጥ መሠረት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን እምነትና ትምህርት ይሰጥ የነበረው በጽሑፍ ሳይሆን በቃል ነው፡፡ የተጻፈም በቃል ሲነገር የነበረው ነው፡፡ “ማመን ከመስማት ነው፣ ማስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ሮሜ 10¸17)፡፡ ከነቢያት እየጻፉ ያስተማሩ መኖራቸው ቢታወቅም ብዙዎቹ በቃል አስተምረዋል፡፡ ሐዋርያትም ጌታችን ወደ ዓለም በላካቸው ጊዜ በቃል አስተምረዋል፡፡ (ማቴ 28¸19፣ ማር 16¸15) ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና ተአምራት ጥቂቱን ብቻ መጻፋቸውን በግልጥ ተናግረዋል፡፡ (ዮሐ 20¸30 ዩሐ 21¸25)፡፡ ራሳቸው ያስተማሩትን ትምህርትና ያደረጉትን ተአምር በሙሉ አልጻፉም፡፡ 2ዮሐ ቁ. 12፡3 ዮሐ ቁ. 13-14)፡፡ ስለ ትውፊት ቅዱሳት መጻሕፍት በብዙ ቦታ ይመሰክራሉ፡፡ (1ቆሮ 11¸2፣23፡፡ 15¸1-3፡፡) 1ተሰ 2¸13፡፡ 2ተሰ 2¸15፡፡

ስለዚህ ቅዱስ …….

አንቀጽ 7 ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስና ድንግልና ቃል ኪዳንና አማላጅነት በሰፊው የታወቀ ነው፡፡ ቅድስና አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኀጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ አሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት መሓል 4¸7 “ምልዕተ ፀጋ ምልዕተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽ” ተብላ በቅዱሳን መላእክት አንደበት በቅድስናዋ ተመሰግናለች ትመሰገናለች፡፡ (ሉቃ 1¸28-30)፡፡ እመቤታችን በውስጥ በአፍኣ በነፍስ በሥጋ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል ማኅደረ መለኮት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ አምላክን ለመውለድ ያስመረጣትና ያበቃት ድንግልናዋ ንጽሕናዋ ነው፡፡ (ሕርያቆስ ቅዳሴ 45 መዝ 132¸13)፡፡ ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው፡፡ ክብረ ቅዱሳን ቅዱስ የሚለው ቃል በግእዝ ንጹሕ ክቡር ልዩ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ቃል ለእግዚአብሔር የባሕርዩ መግለጫ ነው፡፡ እግዚእብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ነውና፡፡ ቅዱሳን የሚለውም ቃል በባሕርዩ ቅዱስ የሆነውን አምላክ ለሚያገለግሉ መላእክትና ደጋግ ሰዎች የሚሰጥ ነው፡፡ መላእክትን ቅዱሳን እንላቸዋለን፡፡ ከማንኛውም ክፉ ነገር የራቁ ሥርዓታቸውን የጠበቁ እግዚአብሔርን ያወቁ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ስለሆኑ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ከመዐርገ መላእክት የደረሱ ደጋግ ሰዎችም በዚሁ የቅድስና ስም ይጠራሉ፡፡

ራሱ ቅዱስ እግዚአብሔርም እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ….. ብሏል፡፡ (ዘሌዋ 19¸2፣ 1ጴጥ 1¸15-16)፡፡ ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃል ሰማዕታት ሁሉ ለቅዱስ እግዚአብሔር ሲሉ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው ስለሰጡ ለስሙ ስለመሰከሩ የተጋድሏቸው በትሩፋታቸው ስላገለገሉ የቅድስናና የብዕፅና ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል ይሰጣቸዋልም፡፡ ጌታችንም በወንጌል “አባት ሆይ በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ ቅዱስ ነው” ብሎ ስለቅድስናቸው ተናግሯል፡፡ (ዮሐ 17¸17) ከእነዚህ ሁሉ በላይ ግን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የቅዱሳን አክሊል የሆነች ቅድስት ናት ስለዚህም ቅድስተ ቅዱሳን ትባላለች፡፡ ሀ/ ክብረ መላእክት ቅዱሳት ተፈጥሯቸው መላእክት በዕለተ እሑድ ከተፈጠሩ ፍጥረታት አንድ ክፍል ናቸው (ኩፋ 2¸6-8)፡፡ የመላእክት ተፈጥሮ ከእሳትና ከነፋስ እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ (3መቃ 2¸10-11) መላእክት አንድ ጊዜ የተፈጠሩና በየጊዜው የማይባዙ ናቸው፡፡ መላእክት በተፈጥሯቸው ነባብያን፣ ለባውያ፣ ሕያዋን፣ ኃያላንም ናቸው፡፡ ሕማምና ሞት የለባቸውም፡፡ የመላእክት ቁጥር በአኃዝ አይወሰንም የብዙ ብዙ ናቸው፡፡ መላእክት በነገድና በአለቃ ይከፈላሉ በነገድ መቶ በከተማ ዐሥር እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ አገልግሎታቸው ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር የቅርብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ዘወትር በዙፋኑ ዙሪያ ሆነው ያመሰግኑታል (ራእ 4¸8-11)፡፡ በተልእኮአቸውም ፈጣኖች ናቸው፡፡ መዝ 103¸4 (ዕብ 1¸6)፡፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለተልእኮ ይወርዳሉ፣ ይወጣሉ፣ ለሰው ልጆችም ይራዳሉ፡፡ (ዮሐ 1¸52፣ ዕብ 1¸14)፡፡ የመላአክት ተልእኮ በጥቅሉ ሲገለጥ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መላላክ፣ የሰውን ጸሎት ምጽዋትና መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ፣ የእግዚአብሔርንም ምሕረትና ቸርነት ወደ ሰዎች ማድረስ ነው፡፡(ዳንኤል 9¸20-22፡፡ ሉቃ 1¸13፡፡ የሐዋ 10¸3-5)፡፡ ሰዎች በሞቱ ጊዜ ነፍሶቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ያቀርባሉ (ማቴ 18¸10፡፡ ዳን 4¸13)፡፡ ለምሕረትም ለመዓትም ይላካሉ (ሮሜ 9¸22)፡፡ በመከራና በችግር ጊዜ ለተራዳኢነት ይላካሉ (የሐዋ 12¸7-11፣ መዝ 89¸7)፡፡

በፍጻሜ ዘመንም ይህ ዓለም በሚያልፍበት ጊዜ ይላካሉ፤ ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ፡፡ (ማቴ 24¸31፡፡ ራእ 7¸1-4) አማላጅነታቸው የቅዱሳን መላእክት አማላጅነትና ተራዳኢነት የሰዎችን ጸሎትና ምጽዋት ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ በተሰጣቸው ባለሟልነት ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ በሰፊው እንደምንረዳው የብዙዎችን ሰዎች ጸሎት፣ መሥዋዕትና ምጽዋት ወደ እግዚአብሔር እያቀረቡ የሚፈልጉትን መልካም ነገር ሁሉ ያሰጣሉ፡፡ ደስታን የምሥራችን ሁሉ ለሰዎች ያበስራሉ፡፡ ደስታን ማብሠር ማጽናናትና የምሥራችን መንገር ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ጸጋ ነው፡፡ (ዘፍ 48¸16፣ ዳን 10¸10-12፣ ሉቃ 1¸13፣ ሉቃ 1¸28-32 ይሁዳ 9)፡፡ የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በቅዱሳን መጻሕፍት በስፋት ይነገራል፡፡ በተለይ በሄኖክ ምዕራፍ 10¸7 እና በዘካርያስ 1¸12፣ ዘጸአ 23¸20-23፣ መዝ 33¸7፣ ሉቃ 1¸28-32 ይሁዳ 9)፡፡ ቅዱሳን መላእክት ንስሓ ገብተው በተመለሱ ሰዎች ደስታ እንደሚያደርጉ በሉቃስ ወንጌል 15¸10 ላይ የተጻፈው ስለ ሰው ልጆች ደኅንነት ያላቸውን ፍቅርና አማላጅነት ያመለክታል፡፡ ክብራቸው ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ባለሟሎች ስለሆኑ ለአምላካቸው ቀናእያን ለነፍሳት ቀዋምያን ስለሆኑ ለምሕረትም ለመዓትም ስለሚላኩ ሰዎችን በችግራቸው ጊዜ ስለሚረዱና ስለሚያማልዱ ቤተክርስቲያን ታከብራቸዋለች፡፡ በስማቸው ጽላት ቀርፃ ቤተክርስቲያን አሳንፃ ድርሳናቸውን አስጽፋ እንዲመሰገኑና እንዲከብሩ ታደርጋለች፡፡ የጸጋና የአክብሮት ስግደት ይሰገድላቸዋል፡፡ (ዳንኤል 8¸15-18፣ ዘፍ 22¸31፡፡ ዘኁል 22¸31፣ ኢያሱ 5¸13-15)፡፡ ለ/ ቅዱሳን ነቢያት ነቢያት በመንፈሰ እግዚአብሔር እየተቃኙ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን እስከ ዳግም ምጽአቱ ተንብየዋል፡፡ ይህንንም ተልእኳቸውን በፈጸሙበት ጊዜ እስከ ሞት ድረስ ፀዋትወ መከራ የተቀበሉ አሉ፡፡ በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያናችን በቅድስናቸው ታከብራቸዋልች፡፡ ቅድስናቸውንም ትመሰክራለች፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን በደሙ ለማዳን እንደሚመጣ በትንቢትና በምሳሌ የተናገሩበትን የተስፋ ዘመን ለማስታወስ “ጾመ ነቢያት” በመባል የሚታወቀው ዘመነ ሱባኤ ከአዳም እስከ ክርስቶስ የተነሡ አበው ነቢያትን ታስታውሳቸዋለች፡፡ ሐ/ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አብ እኔን እንደላከኝ እንዲሁ እኔ እልካችኋለሁ፣ ወደ ዓለም ሁሉ ሄዳችሁ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ አስተምሩ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ…” ብሎ በላካቸው መሠርት ዓለምን ዙረው ያስተማሩና ስለክርስቶስ ስም የመሰከሩ ሐዋርያት ክርስቶስ የመረጣቸውና የቀደሳቸው ቅዱሳን ናቸው፡፡ በሐዋርያት እግር ተተክተው ስለ ስሙ የመሰከሩና የሚመሰክሩ ሁሉ የዚህ ክብርና ቅድስና ወራሾች ናቸው፡፡ መ/ ቅዱሳን ሰማዕታት ስለ ክርስቶስ ስም በዓላውያን ነገሥታት ፊት እየቀረቡ ሳይፈሩና ሳያፍሩ የመሰከሩ በዚህም ምክያት ሕይወታቸውን የሠው ሰማዕታት ቅዱሳን ናቸው፡፡

ሠ/ ጻድቃን ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛና ቢነዳ በነፍሱ ግን ከተጐዳ ምን ይጠቅመዋል? (ማቴ 16¸26)፡፡ ተብሎ በተጻፈው መሰረት ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተው፣ ከዓለም ተለይተው፣ በበዓት ተወስነው፣ ግርማ ሌሊትን ድምፀ አራዊትን ፀብዐ አጋንንትን ታግሠው፣ በምናኔ በተባሕትዎ በገድል በትሩፋት ዘመናቸውን ያሳለፉ፣ ከክፉ ነገር የራቁ፣ ጣዕመ ዓለምን የናቁ የሚታየውን በማይታየው ለውጠው የኖሩ ሁሉ የቅድስና መዓርግ አግኝተዋል፡፡ እነዚህን ስለ እግዚአብሔር ስምና ክብር የተጋደሉ ቅዱሳን ቅድስት ቤተክርስቲያን በዕድሜ በነገድ በፆታ ሳትለይ ለሁሉም በቀኖናዋ መሰረት የቅድስና መዐርግ እየሰጠች ገድላቸውንና የሕይወታቸውን ታሪክ እየጻፈች ያደረጉትንና በየጊዜውም የሚያደርጉትን ተኣምራት እየመዘገበች በስማቸው ጽላት እየቀረፀች ቤተክርስቲያን እያሳነጸች ስማቸውና ክብራቸው የቅድስናም ታሪካቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ሲነገር እንዲኖር አድርጋለች፡፡ ታደርጋለችም፡፡ የቅዱሳን ቃል ኪዳንዳንና አማላጅነት ቅዱሳን በዚህ ዓለም ሳሉ ባደረጉት ተጋድሎ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሙዋልነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ዓለም ሳሉ ሙታንን በማንሣት ድውያንን በመፈወስ አጋንንትን በማውጣት ብዙ የተአምር ሥራ እንዲሠሩ መንፈሳዊ ኃይልና ሥልጣን እንደተሰጣቸው ሁሉ ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ጊዜም ስማቸውን የሚጠራ መታሰቢያቸውን የሚያደርግ በአማላጅነታቸው የሚያምን ሁሉ ዋጋ እንደሚያገኝ ከልዑል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ጻድቁን በጻድቅ ነቢዩን በነቢይ ስም የተቀበለ በክርስቶስ ተከታዮችና አገልጋዮች ስም ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ የሰጠ ዋጋው እንደማይጠፋበት ጌታችን በወንጌል አረጋግጧል፡፡ (ማቴ 10¸41-42)፡፡ ቅዱሳን በዐፀደ ሥጋ ብቻ ሳይሆን በዐፀደ ነፍስም ያማልዳሉ፣ ለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ (ዘጸአ 32¸2-15፣ ሄኖክ 12¸33-400 በነፍስ ሕያዋን ናቸውና (ሉቃ 20¸37-40)፡፡ ረ/ ክብረ ዐፅመ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በገድላቸውና በትሩፋታቸው እግዚአብሐርን አገልግለው ስለ ስሙና ስለ አምልኮቱ መስክረው በሞት የተለዩ ቅዱሳንን ኀፅም ታከብራለች፡፡ በሕይወት ሳሉ በትምህርታቸውና በጸሎታቸው፤ ከሞትም በኋላ በመቃብራቸው ወይመ በዐፅማቸው ላይ የተለያየ ምልክት የታየላቸው ቅዱሳን ኀፅማቸው ከቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ በልዩ ቦታ በክብር እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች በስደት ግዜ ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወርና በግበበ ምድር ሲኖሩ የቅዱሳን ሐዋርያትንና የሰማዕታትን ዐፅም በክብር ጠብቃ ይኖሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በቅዱሳኑ ዐፅም አማካኝነት ተአምሪትን ያሳያል በረከትንና ልዩ ልዩ ፈውስን ይሰጣል፡፡ (2ነገሥ 13¸20-21)፡፡ እግዚአብሔር የቅዱሳንን ዐፅም ለፈውስና ለተለያየ ጸጋ ምልክት ስለሚያደርገው ቤተክርስትያናችን ታከብረዋለች፡፡ ልዩ የክብር ቦታም ትሰጠዋለች፡፡ (መዝ 33¸19-20) ቅዱሳን ደማቸው በፈሰሰበት ዐፅማቸው በተከሰከሰበት ገድላቸው በተፈጸመበት ወዛቸው በነጠበበት ቤተክርስቲያናቸው በታነጸበት ስማቸው በተጠራበት ሁሉ ተአምራት ሲያደርጉ ይኖራሉ የክብራቸውና የቅድስናቸው ምልክትም ይህ ነው፡፡ የቅዱስ እግዚአብሔር ምስክሮች ናቸውና፡፡ (መዝ 33¸20፣ ሉቃ 24¸47)

አንቀጽ 8 ቤተክርስቲያን ቤተክርስትያን የሚለው ቃል ሁለት ፍች አለው፡፡ አንደኛ በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ የምእመናን አንድነት ወይም ማኀበረ ምእመናን ነው፡፡ (ፍት ነገ አን 1፣ ማቴ 18¸17 የሐዋ 20¸28) በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሕዝበ እግዚአብሔር ቤተ እሥራኤል ተብለው ይጠሩ እንደነበሩ በሐዲስ ኪዳን ያሉ ሕዝበ እግዚአብሔም ቤተክርስቲያን ተብለዋል፡፡ ይህም ሕዝበ ክርስቲያን ነገደ ክርስትያን ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ምእመናን የሚሰበሰቡበት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ሐመረ ኖኀ ሐይመተ አብርሃም ደብተራ ኦሪትና መቅደሰ ሰሎሞን ለቤተክርስቲያን ምሳሌዎች ሆነው መሥዋዕት ሲሠዋባቸው አምልኮተ እግዚአብሔር ሲፈጸምባቸውና ስመ እግዚአብሔር ሲቀደስባቸው ኖረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ካለፉ በኋላ የቤተክርስቲያን መሠረትና ራስ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ መሠረተ፡፡ የቤተክርስቲያን አባቶች በጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ በወሰኑት መሰረት ቤተክርስትን “አንዱት ቅድስት በሁሉ ዘንድ ያለች ሐዋርያት የሰበሰቧት” ትባላለች (ጸሎተ ሃይማኖት) ቤተክርስቲያን፡ -    ማኀደረ እግዚአብሔር ናት፣ -    የትምህርት የጸሎትና የአምልኮት ቤት ናት ፣ (ማቴ 21¸13፣ ዮሐ 2¸7 መዝ 68¸9)፡፡ -   

የኃጢአት ማስተሥርያ መስገጃና መማጸኛ ናት፣ -    ወንጌል ይሰበክባታል ቅ/ቁርባን ይቀርብባታል በጥምቀት ልጅነት ይሰጥባታል -    የክርስቲያኖች ዐፅም ያርፍባታል፣ -    በሰዎች መካከል የዕድሜ የነገድ የጾታ ልዩነት ሳይደረግ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥባታል፣ -    ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን የሚያሰኛትና ከሌላው ቤት ልዩ የሚያደርጋት፡- በኤጲስ ቆጶስ (ጳጳሳት) ጸሎትና ቡራኬ ትቀደሳለች በቅብዐ ሜሮን ትከብራለች፣ ታቦተ ሕግ ይቀመጥባታል፣ ምሥጢራተ ቤትክርስቲያን ሁሉ ይፈጸሙባታል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት የቤተክርስቲያን የሕንፃ አሠራር የተለያየ ሆኖ በመሠረተ አቅዋም ሥሦት ክፍል አለው፡- ሀ/ ቅኔ ማሕሌት፡- መዘምራን ስብሓተ እግዚአብሔር ማሕሌተ እግዚአብሔር የሚያደርሱበት ክፍል ነው፡፡ ለ/ ቅድስት፡- የቤተክርስቲያኑ ማዕከላዊ ክፍል ነው ምእመናንም ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉበት በዚሁ ነው፡፡ ሐ/ መቅደስ፡- ታቦተ ሕጉ የሚቀመጥበት መንበር ያለበት ሥጋውና ደሙ የሚፈተትበት ባጠቃላይ ሥርዓተ ቅዳሴው የሚፈጸምበት ዋና ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል መግባት የሚችሉ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ቤተ መቅደሱ ሶስሦት ዋና በሮች አሉት፡፡ ምዕራብ፡ ስብሓተ እግዚአብሔር ይደርስበታል ሥጋውና ደሙ ይሰጥበታል፡፡ ሰሜን፡ ወንዶች ምእመናን ያስቀድሱበታል ካህናት ሰዓታት ያደርሱበታል፡፡ ደቡብ፡ ምእመናት ሴቶች ያስቀድሱበታል ይጸልዩበታል፡፡ በቤተክርስቲያን ጉልላት ላይ መስቀል ይደረጋል የቤተክርስቲያን አርማ መስቀል ነውና፡፡ የመስቀል ምልክት ከሌለው ቤተክርስቲያን አይባልም፡፡ በቤተክርስቲያን በስተምሥራቅ ቤተልሔም በስተምዕራብ ደጀ ሰላም ይገኛል፡፡ ሁሉም የተለያየ አገልግሎት አላቸው፡፡

አንቀጽ 9 ታቦት ታቦት እግዚአብሔር በደብረ ሲና ዐሠርቱ ቃላትን በላዩ ጽፎ ለሙሴ ለሰጠው ጽላት ማደሪያ ማኖሪያ ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን ግን ጽላቱ ታቦት እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህም አዳሪውን በማደሪያው ለመጥራት ነው፡፡ ታቦቱ የጽላቱ ማደሪያ ማኖሪያ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር መገለጫ ነው፡፡ በታቦት ፊት የሚጸለየው የሚሰገደው ዐሠርቱ ቃላት ስለተጻፉበት ብቻ አይደለም እሥራኤል ኃጢአት ሠርተው ሲበድሉ ሲያሳዝኑትና ሲያስቀይሙት ተመልሰው ንስሓ ገብተው ሲያለቅሱና ሲለምኑት እግዚአብሔር እየራራ በቃል ኪዳን ታቦቱ እየተገለጠ ይመራቸውና ያነጋግራቸው ስለነበረ ተቦቱ የምሕረትና የደኀንነት መግለጫም በመሆኑ ነው፡፡ ዘፀ (25¸20-25)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስን ከሰይጣን ጋር አንድ የሚያደርገው ማነው?” ምእመናንንስ ከመናፍቃን ጋር አንድ የሚያደርጋቸው ማነው? የእግዚአብሔርንስ ታቦት በጣዖት ቤት ውስጥ የሚያኖር ማነው? በማለት አስተምሯል፡፡ (2ቆሮ 6¸15-16)፡፡ ከዚህም በላይ ወንጌለዊ ዮሐንስ “ከዚህ በኋላ በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ በመቅደሱም ውስጥ የእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት ታየ” በማለት በራእዩ ገልጿል፡፡ (ራእ 11¸19)፡፡

አንቀጽ 10 ሥርዓተ ጾም ጾም ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከልና የጾም ጊዜ አስኪፈጸም ድረስ ከጥሉላት በዚህም በጾሙ ጊዜ ለተወሰነ ሰዓት ከማንኛውም ምግብ ተከልክለን መጾም ነው፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15፣ ማቴ 6¸15)፡፡ በጠቅላላም ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጐጀውን ነገር ሁሉ መተው ነው፡፡ የጾም ዋና ዓላማም ፈቃደ ሥጋ ለፈቃደ ነፍስ እንዲታዘዝ ለማድረግና በደልን ለማስተሥረይ የነፍስ ዋጋን ለማብዛት ነው፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ስላለው የአፈጻጸሙ ሥርዓት ይለያይ እንጂ ሃይማኖት ላለው ሁሉ ጾም አለው፡፡ ይልቁንም በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ ነበረው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ወራት እህል ውሃ ባፋቸው አይገባም ነበር፡፡ (ዘፀ 34¸28)፡፡ በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰው ሕዝብ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ (ዮናስ 3¸7-10፣ ኢዩ 2¸12-18)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ የሥራ መጀመሪያ አድርጐ የሠራው ሕግ ነው፡፡(ማቴ 4¸2፣ ሉቃ 4¸2)፡፡ ጾም ርኩሳን መናፍስትን የማራቅ ኃይል እንዳለው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ (ማቴ 17¸21፣ ማር 9¸2)፡፡ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም ከመንፈስ------- (የሐዋ ሥራ 13¸2)፡፡ ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙትም በጾምና በጸሎት ነው፡፡ (የሐዋ ሥራ 13¸3፣ 14¸230)፡፡ ደጋግ ሰዎች ሁሉ የፈለጉትን ያዩና ያገኙ በጾምና በጸሎት ፈጣሪቸውን ማልደው ነው፡፡ (ዕዝራ 8¸21፣ ነህምያ 9¸1-3፣ መስቴር 4¸16-17፣ የሐዋ ሥራ 10¸30፣ 13¸2-3)፡፡ የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉም ፈጣሪን መለመኛ የኃጢአት ማስተሥረያ ስለሆነ በጾም ወራት ላምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆነ ሥጋዊ ፍትወትን ከማያበረታቱ ከአልኮል መጠጥ ከሥጋና ከቅቤ ከወተትና ከእንቁላል መከልከል ይገባል፡፡ (ዳን 10¸2-3)፡፡ ጾም በትምህርት በሐዋርያትና በሊቃውንትም ዘንድ ሲሰበክ ኖሯል፡፡ (ፍትሕ መን. አን. 15 ዲድስቅልያ አን. 29)፡፡ ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ንዑድ ክቡር ነው እንደተባለ ጦመኛው ለምሳው ወይም ለራቱ ያሰበውን ወጭ ነዳያንን እንዲረዳበት ለድኩማን ድርጅት ወይም በቤተክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን መስጠት ጾሙን የበለጠ ፍጹም ያደርገዋል፡፡ (ኢሳ 58¸6-11)፡፡ ጾም ከመብላት መከልከል ብቻ ሳይሆን ዐይን ክፉ ከማየት አንደበት ክፉ ከመናገር ጆሮ ክፉ ከመስማት የተቆጠበ እንደሆነ ጾሙን እውነተኛ ጾም ያደርገዋል፡፡ (ማቴ 5¸21-30)፡፡ (ያሬድ ጾመ ድጓ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የራስዋ የሆነ የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፡- የሕጓም መሠረት ሰባት አጽዋማት አሏት፡፡ 1ኛ. ዐቢይ ጾም              4ኛ ገሃድ 2ኛ. ረቡዕና ዓርብ             5ኛ. ጾመ ነቢያት 3ኛ. ነነዌ                   6ኛ. ጾመ ሐዋርያት 7ኛ. ጾመ ፍልሰታ ለማርያም

አንቀጽ  11 ሥርዓተ ጸሎት ጸሎት ሰው በሃይማኖት ፈጣሪውን እያመሰገነና ሥርየት ኃጢአትን እየለመነ ከፈጣሪው ጋር የሚነጋገርበት ቃል ነው፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 14¸528)፡፡ የጸሎት መሠረቱ “እሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል” የሚለው አምላካዊ ቃል ነው (ማቴ 7¸70)፡፡ ለጸሎቱ አፈጻጸምም የተለየ ጊዜና ቦታ አለው በዚህም መሰረት ካህናትና ምእመናን ለጸሎት ወደ ቤተክርስቲያን የሚሔዱባቸው ጊዜያት ጥዋትና ማታ ናቸው፡፡ ጸሎት በ3 ይከፈላል የግል ጸሎት የቤተሰብ ጸሎት የማኀበር ጸሎት ሀ/ የግል ጸሎት የግል ጸሎት የሚጸለየው በቤትና በአመች ቦታ ነው፡፡ የግል ጸሎት ምንም ሳያየውና ሳይሰማው አንድ ሰው በግሉ የጸሎት ቤቱን ዘግቶ በስቂለ ኀሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው አድርጐ በኀቡዕ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡፡ (ማቴ 6¸5-13፡፡ ለ/ የቤተሰብ ጸሎት የቤተሰብ ጸሎት ቃሉ እንደሚያመለክተው አንድ ቤተሰብ በአንድነት ሁኖ የሚያደርገው ጸሎት ነው፡፡ ለዚህም የመቶ አለቃው የቆርነሌዎስ ጸሎት ምሳሌ ይሆናል፡፡ (የሐዋ ሥራ 10¸2-6)፡፡ ሐ/ የማኀበር (የቤተክርስቲያን) ጸሎት የማኀበር ጸሎት የሚባለው ካህናትና ምእመናን ወንዶችና ሴቶች ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድነት ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚጸልዩት ጸሎት ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን የነበሩ አማንያን ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሔዱ ይጸልዩ ነበር፡፡ (1ኛ ሳሙ 1¸9-13፣ መዝ 121¸1፣ ሉቃ 18¸10-14)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያትና የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑት ክርስቲያኖች የቤተክርስቲያን መነሻዎች በሆኑት በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት ማርያም ቤት እንዲሁም በመጀመሪያዋ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን እየተሰበሰቡ ይጸልዩ ነበር (ሐዋ 1¸14-25፣ 3፡1፡12፡12፡13፡1፡3)፡፡ በዚሁ መሰረት በሰንበትና በበዓላት ቀናት ሁሉ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን እየተገኙ በሰዓታት በማሕሌትና በጸሎት ቅዳሴ እንዳያመሰግኑ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አላት፡፡ ሰዓታት በገዳማትና በአድባራት ከዓመት እስከ ዓመት በገጠር አብያተ ክርስቲያናት በእሑድ በበዓላትና በጸሎት ፍትሐት ጊዜ ሌሊት ሰዓታትም አለ (በአጽዋማት ጊዜ በቀን በየሰዓቱ የሚጸለይ (አባ ጊዮርጊስ ሰዓታት)፡፡ ማሕሌት በዝማሜ በመቋሚያ (ዘንግ) በጸናጽልና በከበሮ የሚዘመር የካህናት የኀብረት መዝሙር ነው፡፡ የዐቢይ ጾም ማሕሌት ያለ ጽናጽልና ከበሮ በመቋሚያ ብቻ እየተዘመመ ይዘመራል፡፡ በካህናት መሪነት በምእመናን ተሳታፊነት (ተሠጥዎ ተቀባይነት) የሚፈጸሙ፡ ጸሎተ ቡራኬ ቤተክርስቲያን ጸሎተ ጥምቀተ ክርስትና ጸሎተ ሢመተ ክህነት ጸሎተ ተክሊል ጸሎተ ምህላ ጸሎተ ፍትሐት ጸሎተ ቅዳሴና የመሳሰሉት ናቸው፡፡   ጸሎተ ምህላ ይህ ጸሎት በአገር ላይ  ቸነፈር ጦርነት ሲነሣና ለማኀበረ ሰብእ አስጊ የሆነ መቅሠፍት የተከሠተ ጊዜ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመለስ የምሕረትና የይቅርታ መለመኛ ነው፡፡ (ዘኁ 16¸46-50፣ ትንቢተ ዮናስ 3¸5-10፣ ኢዩ 2 12-19 1ነገ 8¸22-53)፡፡ በመሆኑም የተለየ ችግር ባጋጠመ ጊዜ ምእመናን ሁሉ በየሰበካ ቤተክርስቲያናቸው በጥዋትና በማታ እየተገኙ በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን እንዲለምኑ ቤተ ክርስቲያን ታዛለች፡፡ ጸሎተ ፍትሐት ቤተ ክርስቲያን ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ ታዝዛለች፡፡ ፍትሐት ከዚህ ዓለም በሞት ሥጋ የሚለዩት ሰዎች ከማዕሠረ ኃጢአት እንዲፈቱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ጸሎት ነው፡፡ ጸሎተ ፍትሐት ሥርየተ ኃጢአትን ይቅርታን ዕረፍተ ነፍስን ያሰጣል፡፡ ለደጋጐቹም በክብር ላይ ክብርን ተድላ ዕረፍትን ይጨምራል፡፡ ሙታንና ሕያዋን የሚገናኙት በጸሎት አማካይነት ነው፡፡ “ሕያዋን ለሙታን ይጸልያሉ ሙታንም ለሕያዋን ይለምናሉ” (ሄኖክ 12¸34) በነፍስ ሕያዋን ናቸውና፡፡ (ማቴ 22¸31-32፣ ሉቃ 20¸37-39፡፡ ባሮክ¸3 4)፡፡

አንቀጽ 12 ሥርዓተ ምጽዋት ምጽዋት ከምግባራት ሠናያት አንዱና ዋነኛ ክፍል ነው፡፡ የምጽዋት መሠረቱ እንጀራህን ለተራበ ስጥ፣ ድሆችን በቤትህ አሳድር፣ የቤትህን ርኁብ ቸል አትበል፣ የሚራሩ ብፁዓን ናቸው፡፡ (ኢሳ 58¸6-8፣ ማቴ 5¸7) የሚለው ነው፡፡ ምጽዋት በሁለት ዓይነት መንገድ ይሰጣል፡፡ ሀ/ ቀኝህ የምታደርገውን ግራህ አትወቅ (ማቴ 6¸1-4)፡፡ በማለት ጌታ በአንቀጸ ብፁዓን በተናገረው መሰረት ሌላ ሁለተኛ ሰው ሳያይና ሳያውቅ የሚሰጥ ነው፡፡ ለ/ በፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ 16 እንደታዘዘ በቤተ ክርስቲያን ማዕከልነት የሚሰጥ ነው፡፡ ምጽዋት ወደ ፍጹምነት የምታደርስ ናት (ማቴ 19¸21-22)፡፡ ምጽዋት ከትሩፋት ሁሉ በላይ ናት (ሆሴዕ 6¸6፣ ማቴ 12¸7)፡፡ ምጽዋት ሐዋርያዊ ትውፊትነት አለው (1ኛ ቆሮ 16¸1-4) 2ኛ ቆሮ 9¸6-7፣ ገላ 6¸9-10፣ ዕብ 13¸16)፡

አንቀጽ 13 ሥርዓተ ስግደት ስግደት ሰው አምልኮቱንና ተገዥነቱን ለመግለጥ ራሱን ዝቅ አድርጐ ግንባሩን መሬት በማስነካት ለፈጣሪው ተገዢነቱን የሚገልጽበት ተግባር ነው፡፡ የዚህም መሠረቱ “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ” “በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ” (ዘዳግ 6¸13 ማቴ 4¸10፣ መዝ 28¸2) የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ያለውም ስግደት የአምልኮት ስግደት ይባላል፡፡ የማቀርበውም ለአምላክ ብቻ ነው፡፡ ( 4¸10)፡፡ ለአምላክ የማቀርብ ስግደትም በእውነት በመንፈስ መሆን ይገባዋል፡፡ (ዮሐ 4¸24)፡፡

አንቀጽ 14 ሥርዐተ በዓላት የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለ በዐላት አከባበር የራስዋ የሆነ ሥርዓት አላት፡፡ ከሁሉ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሜንና እሑድን ታከብራለች፡፡ የቅዳሜ መከበር በብሉይ ኪዳን ታዟል፡፡ (ዘፀ 20¸8) በዘመነ ሐዲስ የክርስቲያኖች የቀዳሚት ሰንበት አከባበር እንደ አይሁድ ለሰው የሚከብድ እንዳይሆን ቤተ ክርስቲያን “ኢይደልዎሙ ለክርስትያን ከመ ያጽርኡ ተገብሮ በዕለተ ሰንበት ከመ አይሁድ አላይትገበሩ ከመ ክርስቲያን ወኢትትዓቀቡ ሰንበተ ከመ አይሁድ” (ፍት.መን.አን.19፡፡) በሚለው መሰረት እንዲፈፀም ታስተምራለች፡፡ ሰንበተ ክርስትያን እሑድም ጌታ ከሙታን ተለይቶ ስለተነሣባት የጌታ ቀን ተብላ በሐዲስ ኪዳን የከበረች ዕለት ናት፣ (ራእ 1፡10፡1ቆሮ 16¸1)፡፡

በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጌታ ዐበይት በዐላት ዘጠኝ ናቸው፡፡ እነዚህም ዐበይት በዓላት፡ 1ኛ ትስብእት (ፅንሰብ)                    2ኛ. ልደት 3ኛ. ጥምቀት                           4ኛ. ደብረ ታቦር 5ኛ. ሆሣዕና                            6ኛ. ስቅለት 7ኛ. ትንሣኤ                            8ኛ. ዕርገት 9ኛ. ጰራቅሊጦስ ናቸው፡፡

አንቀጽ 15 ሥዕል ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ የአክብሮት ሥርዐተ ትምህርት አለው፡፡ ሥዕል ከክርስትና በፊት በቤተ አይሁድ የታወቀና ከአምልኮት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን በታቦተ ሕጉ ላይ ስዕለ ኪሩቤን እንዲሥል ራሱ እግዚአብሔር ሙሴን አዞታል፡፡ (ዘፀ 25¸19፡37፡7፣ 1ኛ ነገ 6¸23፣ 2ኛ ነገ 6¸2-17፣ ሕዝ 9¸3፣ 10¸3፣ ሄኖክ 14¸11)፡፡

አንቀጽ 16 መስቀል መስቀል በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ክብር አለው፡፡ መስቀል በነቢያት ትንቢትና ምሳሌ መሠረታዊ ይዘት አለው፡፡ ትንቢት “ሐረገ ወይን ኮነ መድኃኒትየ ዘእምሐሢሦን ይትገዘም ወበጎልጎታ የተከል” (መሐልይ 5¸2)፡፡ “ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፍርሁከ፡ ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት፡ ወይድኀኑ ፍቁራኒከ” (መዝ 59¸4 ተብሎ ተነግሯል፡፡)   ለምሳሌ የኖኀ መርከብ የተሠራችበት እንጨት፡፡ (ዘፍ 7¸6)፡፡ ሙሴ የፈርዖን መሰግላንን ድል ያደረገበት በትር፡፡ (ዘጸአ. 4¸2-9 አርዌ ብርት ዘኁል 21¸9)፡፡ የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ከጌታችን መድኃኒታችን ከኢየሱስ ከርስቶስ ስቅለት በፊት መስቀል የመቅጫ የርግማንና የውርደት ምልክት ነበር፡፡ (ዘዳግ 21¸23፣ 2ኛ ቆሮ 5¸21፣ ገላ 3¸13)፡፡ ከጌታችን ከመድኃነታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በኋላ ግን የክርስቶስ መስቀል የመንፈሳዊ ነፃነታችን ዓዋጅ የተነገረበት ሰላማዊ ዙፋን፡፡ (መዝ 2¸6 እና 7፡44፡4) ስለሆነ ለክርስቲያናች ሁሉ የነፃነትና የድል ምልክት ነው፡፡ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” ክርስቶስ ሰላምን ነፃነትን በመስቀሉ አደረገ፡፡ (ኤፌ 5¸15-17)፡፡

አንቀጽ 17 ንዋያተ ቅድሳት ንዋያተ ቅድሳት ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለመፈጸም የሚያስችሉ የከበሩ ንዋያት ናቸው፡፡ ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን አፈጻጸም አገልግለት የሚውሉ የተለያዩ ንዋያተ ቅድሳት አሉ፡፡ እነዚህም፡- ጻሕል ጽዋዕ ዕርፈ መስቀል ማሕፈድ መሶበ ወርቅ ጽንሐሕ ቃጭል አትሮንስ የመቀደሻ የካህናትና የዲያቆናት አልባሳት ካባ ላኀቃ፡፡   አባ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ 2005 ዓ.ም

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org