የተከበረውን አካል እንጠበቀው

 

ሴቶችን ማስገረዝም ሆነም በሴቶች ላይ ጥቃት ማካሄድ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚወገዝ መሆኑን የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ በየትኞቹም የቤተክርስቲያኗ መጻሕፍት ሴት ልጅ ትገረዝ፣ጾታዊ ጥቃትም ይድረስባት የሚል ትእዛዝም የለም፤ ከየትኞቹም አባቶች የተላለፈ ትምህርትም የለም፡፡ ችግሩ በአጭር እንዲቋጭ  ቤተ ክርስቲያኗ ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥታለች፡፡ ጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ/ም ስለዚሁ ችግርና መፍትሔዎች የሚያትቱትን መጻሕፍት በማስመረቅ  እና የአቋም መግለጫውን በማውጣት ለሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ርክክብ አድርጋለች፡፡

 በተለያዩ ጊዚያት ስታስተምር የቆየች ብትሆንም መመሪያ ተዘጋጅቶ፣ ከመንግሥት አካላትና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በይፋ መንቀሳቀስ የጀመረችው   ከተጠቀሰው ዕለት አንስቶ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መወገድ እንደመፍትሄ የተወሰደውም ኅብረተሰቡን በተለይም እናቶችን ማስተማር እንደሆነ  ታምኖበታል፡፡ ትምህርቱንም በባለቤትነት ተረክበው ማስተማር የሚኖርባቸው የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ሊሆኑ እንደሚገባ ግንዛቤ ላይ ተደርሶ በእነሱ አማካይነት እነሆ ሥራው በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

 

ነገር ግን በመላ ሀገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየውን ይህንኑ ችግር በአንዴ ማስወገድ የማይቻል በመሆኑ መጀመሪያ ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸውን ቦታዎች ማጥናት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ተከናውኗል፡፡ የተመረጡትም ቦታዎች በሰሜን ሸዋ ዞን (ደብረ ብርሃን አካባቢ) በሚገኙ አምስት ወረዳዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የካና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ናቸው፡፡

 

ለችግሩ መወገድ ቤተክርስቲያን ለምታደርገው እንቅስቃሴ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ያደረገው ደግሞ የኖርዌ ቤተ ክርስቲያን ተራድኦ ነው፡ ይህ ምግባረ ሠናይ ድርጅት የሴት ልጅ ግርዛትና ጾታዊ ጥቃት እንዲወገድ ጥረት ከማድረጉም በላይ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የድህነት መንስኤዎች ተወግደው ልማት እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡እስከዚህ ድረስ ሁኔታውን ከገለጽን አሁን ደግሞ በተጠቀሱት ቦታዎች የተሠሩትን ሥራዎች በመጠኑ እንግለጽ፡፡

 

የሰሜን ሸዋው እመርታ

ችግሩን ለመፍታት ተገቢውን ሥልጠና በተገቢው ወቅት ለሚገባቸው ሰዎች መስጠት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ለማንኛውም ጉዳይ ትምህርትና ቅድመ ሥልጠና አስፈላጊ መሆኑን ያስተማረው የፍጥረታት ባለቤት መጋቢና አስተዳዳሪ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ትመሰክራለች፡፡ ወንጌል ለሁሉም ፍጥረታት የተስፋፋው ጌታችን ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ለደቀመዛሙርቱ የሚገባቸውን ትምህርት ከሰጣቸው በኋላ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ  ኅብረተሰቡን በማስተማር ችግሮችን ለመቅረፍ ትጠቀምበታለች፡፡ በየትኛውም ቦታ እንደሚደረገው በዚሁ ሥፍራም መጀመሪያ ለካህናቱ በተለይም ግርዛት ለሚፈጽሙ ሰዎች እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ላላቸው ግለሰቦች ሰፊ ሥልጠና እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ ከዚያም የተማሩትን ትምህርት በመገንዘብ ለሌሎች ሰዎች ማስተማር እንደሚገባ ተወስኖ ትምህርቱ መሰጠት ተጀመረ፡፡ሥልጠናውና ትምህርቱ ከተሰጣቸው ግለሰቦች መካከል አቶ አስገልጤ አንዱ ናቸው፡፡

 

አቶ አስገልጤ በዚሁ ዞን የመቀኝ ቀበሌ አካባቢ ተወላጅ እና ነዋሪ ሲሆኑ በአካበባቢው ከተከበሩና ተደማጭነት ካለቸው ጥቂት ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ቀደም ሲል ሴቶችን  ይገርዙ አንደነበር፣ ትምህርቱ ከተሰጣቸው በኋላ ግን ድርጊቱን ከማውገዛቸውም ሌላ ሌሎችንም በማስተማር ብዙዎችን ማስተዋቸውን ይናገራሉ፡፡ “ሴቶችን በመግረዝ ከፍተኛ በደል በማድረሴ በመጀመሪያ ንስሓ ገባሁኝ፤ ለንስሐ ያበቃኝም ዋናው ነገር የሴትን ልጅ ግርዛት አስከፊነት በተንቀሳቃሽ ፊልም ተዘጋጅቶ በቀረበልን ዕለት ነበር፡፡ የሚገርመው በምገርዝበት ወቅት ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ ለማወቅ አለመቻሌ ነበር፡፡ ፊልሙን ሳየው ግን ራሴን ጠላሁ፤ የሰው ደም በማፍሰሴም ተጸጸትሁ፤ ድርጊቱን የሚያደርሱትንም ለማወገዝ ለራሴ ቃል ገባሁ፤ ከዚያን ሰዓት ጀምሮም በመንገዴ ያገኘኋቸውን ሰዎች ስለግርዛት አስከፊነት በመግለጽ ማንም ሰው እንዳይፈጽመው በእግዚአብሔር ስም ቃል እያስገበሁ ወደቤቴ ሄድኩኝ፡፡”

 

በደብረ ብርሃን ዙሪያ የከተራ ቅዱስ እስጢፋኖስ ካህን የሆኑት ቄስ መንገሻ ደሴ እንደተናገሩት “ ሴቶች እንዳይገረዙ፣ ጾታዊ ጥቃትም እንዳይደርስባቸው ያገዘን በተለያዩ የጽዋ ማኅበራትና በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የምናስተላልፈው መልእክት ነው፤ እኛ ካህናት በነገሩ ካመንን ኅብረተሰቡን ማሳመን አያዳግተንም፤ ኅበረተሰባችን እኛ የምንለውን ይቀበላል፤ ያምናልም፡፡ መሠረታችን ቅዱስ መጽሐፍ ስለሆነ ሕዝቡም እኛን የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል አስተላላፊዎች መሆናችንን ስለሚያውቅ አታድርጉ ካልን አያደረግም፣ አድርጉ ካልነው ደግሞ ይፈጽማል፡፡ በመሆኑም አሁን ሁሉም ባይባልም አብዛኛው ሰው አያስገርዝም፡፡” ከዚህም በተጨማሪ እናቶች በወለዱ በሰባተኛው ቀን የንሥሐ አባታቸውን ቄስ ጠርተው ቤታቸውን ጠበል ያስረጫሉ፤ ቄሱም ጠበል ከመርጨታቸው በፊት የተወለደችው ሕፃን ሴት መሆኗን አረጋግጠው ላያስገርዙ ቃል ያስገቧቸዋል፡፡ እናቶች የራሳቸውን ልጆች ብቻም ሳይሆን ሌሎች እናቶችም እንዳያስገርዙ የቄሱን ቃል እንዲናገሩ በእግዚብሔር ስም ቃል ይገባሉ፤ በዚህን ጊዜ የተነገራቸውን ቃል ለማስተላለፍ እረፍት የላቸውም፤ የአካባቢያችን ሕዝብ የእግዚአብሔርን አደራ ተሸክሞ መቀመጥ እግዚአብሔርን እንደመዳፈር ይቆጠራልና፡፡ እንግዲህ እነዚህንና ሌሎች የማስተማሪያ ስልቶችን በመጠቀም ችግሩን መቅረፍ እየተቻለ መሆኑን ቄስ መንገሻ ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡

 

የችግሩን አስከፊነት በመገንዘብ ሥልጠናውን ወስደው የበኩላቸውን ጥረት ያደረጉት ደግሞ ዲያቆን መግራ ጣሰው ናቸው፡፡ በዞኑ የአንጎለላ ወረዳ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አስተባባሪ የሆኑት ዲያቆን መግራ ለችግሩ መወገድ ያደረጉትን ጥረት እንዲህ ይገልጹታል፡- “ ችግሩ በተለይ በገጠራማው አካባቢ ስለሚፈጸም በአብዛኛው የገጠር ልጆችን በመሰብሰብ ትምህርቱን እንሰጣለን፤ ትምህርቱን የምንሰጠው በቡድን ሲሆን ግልጽ ውይይትም ይደረጋል፡፡ በውይይቱ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ ወንድ እንጂ ሴት ልጅ የማትገረዝ መሆኗን እናስተምራለን፡፡ ከዚያም ትምህርቱን በሚገባ የጨበጡት ተማሪዎች ወላጆቻቸው ሴት ሕፃናትን እንዳያስገርዙ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሱ እንዲያስተምሯቸው ይደረጋል፡፡ ቀስ በቀስ ሐሳቡን በመቀበል ድርጊቱን እንዲያቆሙ ይደረጋል፤ በዚህም ውጤታማ ሆነናል ሲሉ ዲያቆን መግራ ተናግረዋል፡፡

 

የሽሮሜዳው ግርዛት ገጽታ

እስከአሁን በሰሜን ሸዋ የነበረውን ለግንዛቤ ያህል በመጠኑ አቅርበናል፡፡ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ንዑስ ሥፍራ በሆነችው እና በተለምዶ  ሽሮ ሜዳ እየተባለች በምትጠራው አካባቢ በዚሁ በኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ተራድኦ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ አድራጊነት በመደረግ ላይ የሚገኘውን የሴት ልጅ ግርዛትና ጾታዊ ጥቃት ማስቆምን እንመልከታለን፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሴት ልጅ ግርዛት የቀረ የሚመስላቸው ሰዎች እንዳሉ በተለያዩ ጊዚያት አጋጥመውናል፡፡ እውነታው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የኢትዮያጵያ ጎጂ ልማዳዊያን ድርጊቶች አስወጋጅ ማኅበር አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ልማት ድርጅት የተባለው  ያጠናው አኅዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 52 ፐርሰንት የሚሆኑት ሴት ሕፃናት ይገረዛሉ፡፡ በተለይም ይኸው ችግር ጎልቶ የሚታየው በጉለሌና በየካ ክፍለ ከተሞች መሆኑም መረጃው ይጠቁማል፡፡ ለዚህም ነው የኖርዌ ቤተ ክርስቲያን ተራድኦ ሰቆቃው የበዛባቸውን ሥፍራዎች በመምረጥ የማስወገዱ ሥራ እንዲካሄድ ያደረገው፡፡ ይህ ምግባረ ሠናይ ድርጅት እንደሚያምነው ችግሩን ለማስወገድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባላት ተደራሽነትና በካህናቷ አማካይነት ከፍተኛ ሚና እንደምትጫወት ተገንዝቦ እነሆ የማስቆሙ ሥራው በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

 

ሥራው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማየትም ጥቅምት 10 ቀን 2006 ዓ/ም በሽሮ ሜዳ ወረዳ ውስጥ ሱላህ ገነተ ኢየሱስ የሚባለው የጽዋ ማኅበር ችግሩን ለማስወገድ እያከናወነ ያለውን ሁኔታ በቦታው በመገኘት ተመልክተናል፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ቤተ ክርስቲያኗ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ተያያዥ ችግሮችን ለማስወገድ አንድ መምሪያ አቋቁማ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሥር ሆኖ እነዚህንና መሰል የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ የተቋቋመው ይኸው መምሪያ ከሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች አንዱ የሴት ልጅ ግርዛትንና ጾታዊ ጥቃትን ማስወገድ እንደሆነ ከፍ ብሎ ተጠቅሷል፡፡ መምሪያውም ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ የጽዋ ማኅበር መሆኑንም በዚህ ጽሑፍ ተጠቅሷል፡፡ የሽሮ ሜዳው የጽዋ ማኅበርም ከሚጠቀሱት የጽዋ ማኅበራት አንዱ ነው፡

ማኅበሩ የተቋቋመው በ1983 ዓ/ም ቢሆንም ከመምሪያው ጋር መሥራት የጀመረው ግን ከግንቦት 2004 ዓ/ም ጀምሮ እንደሆነ በመምሪያው የሴት ልጅ ግርዛትና ጾታዊ ጥቃት ማስቀረት ፕሮጀክት አስተባባሪ መምህር ዘላለም አሰፋ ገልጸዋል፡፡ መምህር ዘላለም እንደገለጹት ማኅበራት ችግሩን በቀላሉ ለማስወገድ የሚችሉ መሆኑን በማወቃችን ይህንን ማኅበር አንዱ የሥራችን ቁልፍ አካል በማድረግ በመንቀሳቀሳችን ከፍተኛ ውጤት አምጥቷል ብለዋል፡፡ በዕለቱ ለገኙት የጽዋ ማኅበር አባላት መምህር ዘላለም ስለሁኔታው ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን በመጥቀስ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ርእሱም"ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሪያለሁና አመሰግንሀለሁ' መዝ-139፤14የሚል ነበር፡፡ ርእሱን ሲያብራሩም “አግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ሁሉንም ነገር አሟልቶና አስተካክሎ ፈጥሮታል፡፡ ታዲያ በሥራው የምናምን ከሆነ ለሴት ልጅ አሟልቶ የሰጣትን ገላ በስለት የምንተለትልበት ምክንያቱ ምን ይሆን ሲሉ ጠየቁ፤ የፈጠረው ሁሉ የተሟላና የተስተካከለ፣ነውር፣ ነቀፌታ የለበትም፡፡ ይህንን የምናምን ሰዎች ሴቶችን ለምን እንገርዛለን;፤ እናስገርዛለንም ;፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራን መፈታተን አይሆንምን ሲሉ ጠየቁ፡፡ በእኛ በደካማው አእምሯችን አንተ ከፈጥርከው የሴቶች አካል ውስጥ አንድ የማያስፈልግ ትርፍ አካል ስላለ በስለት ተቆርጦ መጣል አለበት እንደማለት ነው፡፡

 

መምህር ዘላለም አክለው ሲናገሩም ይህ አካል ከሌሎች አካላት እጅግ የከበረ፣  በልብስ የተሸፈነ፣ትውልድም የሚገኙበት በመሆኑ ሊቆረጥ የማይገባ   የእግዚአብሔር የእጅ ሥራ ነው፡፡

በሴት ልጅ ብልት ላይ የሚገኘው አካል ትርፍ ስለሆነ ይቆረጥ እያልን መሆናችንን ታስተውሉታላችህን?” በማለት አባላቱን ሲጠይቁት፡- አውነት ነው ሴትን የሚገርዝ ሁሉ አምላክ ተሳስቷል ያሰኛል ሲሉ በጭብጨባ አረጋግጠዋል፡፡ መምህር ዘላለምም ታዲያ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ የምንቀበል ከሆነ ሴቶችን ላለማስገረዝ ቃል ግቡልኝ ሲሏቸው አባላቱም ቀድሞ ሴት ልጆቻችንን እንዳናስገርዝ ቃል የገባነውን ቃላችንን እንጠብቃለን ሌሎችም እንዳያስገርዙእናስተምራለን፤ በማለት በድጋሚ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ቦታው ስላልሆነ እንጂ በምስልና በድምጽ ተቀርጾ ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆን  ተብሎ ተቀምጧል፡፡

 

የዚሁ ማኅበራት አባላት ትውልዳቸው በጋሞጎፋ ዞን [S1] ሱላህ የሚባል ወረዳ ሲሆን አንድነታቸውን ላለመተውና ባህላቸውን ለማሳደግ እንዲሁም ማኅበራዊ ኑሯቸውን ለማጠናከር ከ1983 ዓ/ም ጀምሮ የተቋቋመ መሆኑም ከዚህ በላይ ተጠቅሷል፡፡ በትውልድ አካባቢያቸውም ገነተ ኢየሱስ የሚባል ቤተ ክርስቲያን አሠርተው እምነታቸውን በማስፋፋት ላይ መሆናቸውን የማኅበሩ መሥራችና አባል የሆኑት እና በዋናነት በካሜራ ባለሙያነት የሚተዳደሩት አቶ ታምሩ ገልጸውልናል፡፡ አቶ ታምሩ እንደሚሉት “እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በትውልድ ቀያችን ቤተ ክርስቲያን ስላልነበረ አባቶቻችን፣ ታናናሽ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን የሚያመልኩበት አጥተው ግማሹ በባዕድ አምልኮ፣ ገሚሶች ደግሞ የሌላ እምነት ተከታዮች ሆነው ቀርተዋል፡፡  እንዲያው እነሱ የእኛ ባላንጣዎችም ለመሆን ሞክረዋል፡፡ ሁኔታው ስላሳዘነን ሕዝባችን ይዳን በማለት ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ወስነን እነሆ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል” ሲሉ አቶ ታምሩ በደስታ ይናገራሉ፡፡

 

አቶ ታምሩ ስለነበረው ችግር ሲያስታውሱ “ቤተ ክርስቲያኑን ለማሠራት የአካባቢው ሕዝብ በሌሎች እምነቶች ስለተወሰደ ክፉኛ ተፈታትነውናል፤ለማስፈረስም ቀስት ወርውረውብናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን የያዘ ሰው ምንም ስለማይሆን አሸንፈናቸዋል” ሲሉ በኀዘን መንፈስ ተናግረዋል፡፡

 

የሴት ልጅ ግርዛትንና ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ በትውልድ ቀያቸው ስላለው ሁኔታ አባላቱን ጠይቀናቸውም ነበር፡፡ ሲመልሱም ችግሮች አሁን ድረስ ይካሄዳሉ፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኑን ለማሠራት ስለምንሔድ አስከፊነቱን በስፋት እናስተምራለን፡፡ ምንም አንኳ ሙሉ በሙሉ ተቀብለው በአንዴ ማስቆም ባይቻልም ድሮ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁን በእጅጉ ይሻላል፡፡ በመንግሥት ቅስቀሳ፣ በቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮና እኛም በምናደርገው  ጥረት ከሚገረዙት የማይገረዙት እየበዙ ነው፡፡

 

በሽሮ ሜዳ ስላለው የሴት ልጅ ግርዛትና ጾታዊ ጥቃት አባላቱ እንዲነግሩን ጠይቀናቸው እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:-“ በአሁኑ ሰዓት የሚያስገርዙ ሰዎች ተመናምነዋል፤ ግርዛት በወሊድ ጊዜ የሚያስከትለው አደጋ እስከሞት የሚያደርስ መሆኑን በተደጋጋሚ በብዙሃን መገናኛና በሌሎች አካላትም ስለተነገረን ሁላችንም ድርጊቱን አውግዘነዋል፡፡” አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ለማኅበራችን መጠናከርና የድርጊቱን አስከፊነት ለማስተማር አንድ መምህረ ንሥሓ ስለተመደቡልን በጣም ደስ ብሎን ትምህርቱን ለሌሎች እህቶችችን በማስተማር ላይ እንገኛለን፡፡”                

ማኅበሩ በኮሚቴ የሚመራ ሲሆን ኮሚቴዎችም ከሽሮ ሜዳ እስከ ትውልድ ቀያቸው በመንቀሳቀስ ኅብረተሰባቸውን በማስተማር ላይ መሆናቸውንም በዕለቱ ገልጸውልናል፡፡ እኛም በነገሩ ሁሉ ስለተደሰትን ማኅበሩ እንዲጠናከር፣ በቀያቸውም ሆነ አሁን በሚገኙበት ሥፍራ ሆነው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያናችን ከጎናቸው እንደምትቆም በማረጋገጥ የዕለቱን መርሐ ግብር በዚሁ አጠናቀቅን፡፡

 

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ

 

 

Contact Us

Tel. +251111553566/ +251111563033
Fax: +251111551455
P.O. Box: 503 Addis Ababa, Ethiopia
E-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it., This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Web site: www.eotcdicac.org