Skip to main content

  “ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር” ABGELAUFEN SEIT 10.04.2020

  11.04.2020 Media info Top news
  “ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር”

  በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፡፡ እግዚአብሔር መስክሮለት የመጣ ጌታ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ “ባክናክሙ እምቤተ እግዚአብሔር” በእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ እግዚአብሔር እግዚህ አስተርአየ ለነ፡፡ በምልአት ያለ እግዚአብሔር በረድኤት በሥጋ ተገለጠ፡፡

  ይህ መዝሙር የእሥራኤል ሕዝብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በደስታ በእልልታ ሲቀበሉት የዘመሩት መዝሙር ነው፡፡

  ሆሣእና ማለት (በሒብሩ ቋንቋ) እባክህን አድነን ማለት ነው ሆሣእና ለወልደ ዳዊት የዳዊት ልጅ እባክህን አድነን ማለት ነው፡፡ እኛም አሁን አድነን ልንለው ይገባል፡፡ በእግዚአብሔር ስም ማለትም እግዚአብሔር ነኝ ብሎ የመጣ እርሱ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል ነው፡፡

  “ወበዊኦ ኢየሩሳሌም ተሐውከት ኩሏ ሀገር እንዘ ትብል መኑ ውእቱ” ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ይህ ማነው ብለው ከተማይቱ ታወከች ማቴ. 21÷12 ላይ

  “ወሶቤሃ ፈነወ እግዚእ ኢየሱስ ፪ቱእም አርዳኢሁ” ያን ጊዜ ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ በፊታችሁ ወዳለች አገር ሂዱ ያን ጊዜ አህያ ከነውርንጭላዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ፡፡ ፈታችሁም አምጡልኝ አላቸው አዎ ሰው ሁሉ ከማዕሰረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜ እንደ ደረሰ ለማጠየቅ፡፡ “ወዝ ኩሉ ዘኮነ ከመ ይትፈጸም ዘተብህለ በነብይ በልዋ ለወለተ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ ጻድቅ ወየዋህ ይመጽእ ሃቤኪ እንዘ ይፄአን ዲበ ዕድግት ወዲበ እዋላ፡፡”  

  ጻድቅ የባሕርይ አምላክ የዋህ፣ ኃዳጌ፣ በቀል ንጉስሽ (በእዋል) በዕድግት ተቀምጦ ይመጣል ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገሯት ብሎ ነቢዩ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡

  ደቀ መዛሙርቱ ሂደው እንደ አዘዛቸው አመጡለት (ወረሃኑ አልባሲ ሆሙ ላዕሌሆን) ልብሳቸው ጐዘጐዙለት ከበቴ አበሳ ይቅር ባይ ነህ ሲሉ ነው፡፡

  images (2)-1

  “መስማትን ትሰማላችሁ፤ አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ አትመለከቱም”፡፡

  ነቢዬ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ ይህን ትንቢት የተናገረ የክርስቶስን ትምህርት አንቀበልም ላሉና ላላመኑበት ቤተ አይሁድ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን የነቢዩ ኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ የወቀሰው አይሁድን ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አምላክ ነኝ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ቢላቸው፣ ወልደ ዮሴፍ አሉት፣ ዕሩቅ ብእሲ አደረጉት፤ ስለዚህ ነቢዩ ኢሳይያስ “መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉም” ያለው ጌታ ወንጌል ሲያስተምር ትምህርቱን ተቀብሎ ለማመን ሳይሆን ለማሽሟጠጥና የክስ ነጥብ ለማግኘት ሲሉ ቤተ አይሁድ ከጉባኤው አይለዩም ነበር፤ የሚያስተምረውን ሁልጊዜ ይሰማሉ፤ ነገር ግን አያጤኑትም፤ አያዳምጡትም፤ አያስተውሉም፤ ወደ አእምሮአቸው አያስገቡትም፤ “ማየትንም ታያላችሁ፤ አትመለከቱም” ያለው ድውይ ሲፈውስ ለምፅ ሲያነጻ፣ አጋንንት ሲያወጣ፣ አንካሳ ሲያበረታ፣ ዕውር ሲያበራ እያዩ “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል፤ በሰንበት አልጋ አሸክሞ ይሰዳል እያሉ ይሰድቡት፣ ይወነጅሉት ነበር እንጂ” ድውያነ ሥጋን ፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት ሲፈውስ እያዩ አላመኑበትም፡፡

  ባለማመናቸውም ከፍዳ አልዳኑም፤ በሥጋቸውም፣ በነፍሳቸውም በሽተኞች ነበሩ፤ አልተፈወሱም፡፡ በዛሬው ዕለት “ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” እያሉ ሕዝቡ ሽማግሌዎችና ሕፃናት ዘንባባ ይዘው ሲያመሰግኑት “ሕፃናቱን ዝም በሉ በላቸው ለምን ይንጫጫሉ?” የሚል ተቃውሞ ነው ያቀረቡት የአይሁድ ካህናት፡፡ ጌታም “ከሕፃናትና ከልጆች አንደበት ምስጋናን አዘጋጀ”፡፡

  “እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎ ስብሐተ” ከሕፃናት አንደበት ምስጋናን ተቀበልህ ማለትም በእነዚህ አንደበት ተመስገን አው የአርባ - የሰማንያ - ቀናት ዕድሜ የነበራቸው እንዲሁም የዓመት የሁለት ዓመት ዕድሜ የሆናቸው እነዚህ በዕለተ ሆሣእና ዕጉለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዘው ሆሣእና በአርያም እያሉ አመስግነውታል፡፡

  “ጥበብ ከሠተት አፈ ሕፃናት ወልሳነ በሐማን ረሰየት ርቱዐ ወነባቤ” ከእንስሳት ሁሉ አህያ የተመረጠችበት ምክንያት አህያ ትዕግሥተኛ፣ አደጋንና መከራን ቻይ፣ ትህትና ያላትና በጣም ከሌሎች እንስሳት የተለየች የዋሂትና እነዚህ ገጸ ባሕርያት ለጥሩ በእምነት በሃይማኖት ለሚኖሩ  ክርስቲያኖች ነው፡፡ “መስዋዕቱ ለእግዚአብሔር መንፈስ የዋህ” የእግዚአብሔር መስዋዕቱ የዋህ ልቡና የየዋህ ሰው ልቡና ነው፡፡ መዝ. 50÷17

  በሕይወታችን ሁሉ ትህትና፣ ፍቅር፣ ትእግስት ርኅራኄ ያስፈልጋል፡፡

  ፀላኢ ገፋኢ የሚሆን ዲያብሎስን ትረታው ትመታው ዘንድ አስተዳሎከ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የሰውን ልቡና እንደዙፋን ሰውነቱን እንደ ድንኳን ፍትወታት እኩያት ኃጣውእን እንደ አጥር አድርጐ ይገዛ የነበረውን ቢፅ ሓሳውያን ትረታው ዘንድ ትመታው ዘንድ ነው፡፡

  “ብፁዓን እለ ንጹሐን በፍኖቶሙ” በሃይማኖት በምግባር ንፁሓን የሆኑ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡

  “ወእለ የሐውሩ በሕገ እግዚአብሔር” እግዚአብሔር አምላክ በሠራቸው ሕግጋት ጸንተው የሚኖሩ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡ አምልኮቱን የሚሹ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡ መዝ. 8÷2

  መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሔኖክ ሲመሰክር አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ዘፍ. 5÷22

  የሔኖክ አካሔዱ አኗኗሩ ስናይ ሕገ እግዚአብሔርን የሚጠብቅ ታላቅ የእምነት ሰው አሰኝቶታል በዚሁም አካሔዱ ማቱ ሳላን ወለደ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በላይም የኖረ እኛ ዛሬ ለ60 እና ቢበዛ 80 ዓመታት እነዛም ዘመናት እንዲያሙ ስቃይ ሐዘን በሽታ ሰቀቀን የበዛባቸው ናቸው፡፡ ዕብ. 11÷5

  የሕይወት መቀጠልና አለመቀጠል ጉዳይ ጤና ሲታጣና ሲታወክ በመንፈስ ላይ ሊያስከትለው ስለሚችለው ጉዳት እንዲሁም ደግሞ የመንፈስ መታወክም በሰውነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የተረጋገጠና የታመነ ነው፡፡ መንፈሳቸው የታወከና በሀሳባቸው ብዙ አስጨናቂ ነገር የሚመላለስባቸው ብዙም የሚያስቡና የሚሰጉ የሚጨነቁም የኅሊና ጸጥታ የሌላቸው ሰዎች ሁሉ ያለ ጊዜያቸው ሲወድቁ በራሳቸው ይታያሉ፡፡

  ለምን ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም ርቋል (በጣም የራቀ ነው) በከንቱም ያመልከኛል፡፡ ማቴ. 15÷8

  ነገር ግን ሕግን መተላለፍ መቅሰፍትን ያመጣል ሮሜ 4÷15

  ይህ አመጸኛ ትውልድ ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፣ የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታው፡፡ ዘኁ. 11÷33

  የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ / ታፈርሳላችሁ አይጠቅማችሁም ትጎዳላችሁ፡፡ እግዚአብሔር ከእናንተ ሕግን ከሚያፈርሱ መካከል አይደለምና፡፡ ዘኁ. 14÷41

  ሥጋዊ ምኞትን ብቻ መከተል የእግዚአብሔር ሕግ በመዘንጋት ከመሆኑም በላይ ሁል ጊዜም ለዚሁ ለሥጋችን ብቻ እዚህም እዚያም መሯሯጥ የቱን ያህል የመንፈሳዊውን ደረጃ ዝቅ እንደሚያደርገውና የሞራልንም ኃይል እንደሚሰብረው የሚያስከትለውን ጉዳት የቱን ያህል ከፍተኛ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡

  ጠንካራ ሕዝብና እውነተኛ እምነት

  ሰዎች እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡

  ዓመፃ ሁሉ ግፍ መመኘት ክፋት ሞላባቸው ቅናትን ነፍስ መግደልን ክርክርን ተንኰልን ክፉ ጠባይን ተሞሉ የሚያሾከሽኩ ሐሜተኞች አምላክን የሚጠሉ የሚያንገላቱ ትዕቢተኞች ትምክህተኞች ክፋትን የሚፈላለጉ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፡፡

  የማያስተውሉ ውል የሚያፈርሱ ፍቅር የሌላቸው ምሕረት ያጡ ናቸው እንደዚህ ለሚያደርጉ ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ሮሜ 1÷28

  አንድ ሕዝብ በሌሎች ወገኖች ዘንድ ተፈርቶና ተከብሮ ነጻነቱን እንደጠበቀ ሊኖር የሚችለው እምነቱና መንፈሱ ከፍተኛ ሆኖ ሲገኝና በምንም ዓይነት አኳኋን ሊበገር የማይችል ጠንካራ የሞራል ኃይል ያለው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የሆነ ሕዝብ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ሃይማኖት የሌለው ሕዝብ ልቡ ፍርሃትን የተመላ ለሰዎች ንፁህ ልብ ፍቅርና ርኅራኄ ደግነትና ትዕግሥት የሌለው ነው፡፡

  በበደልነው በደል ሁሉ ጌታ ሆይ በድለናል ስንፍና አድርገናልና እባክህ ኃጢአት አታድርግብን ልንል ይገባል፡፡ በድለናልና እግዚአብሔር አምላክ መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች ሸክም ሆነውብኛል ልታገሣችሁም ደክሜአለሁ፡፡

  እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ አይኔንም ከእናንተ እሰውራለሁ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፡፡ እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋልና ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንዳንድ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ ክፉ ማድረግ ተው፡፡ ት.ኢሳ. 1÷14

  እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ የባርነታችሁ ቀንበርን ሰብሬአለሁ ቀና ብላችሁ እንድትሔዱ አድርጌላችኋለሁ ነገር ግን ባትሰሙኝ ትእዛዜንም ሁሉ ባታደርጉ

  ሥርዓቴንም ብትንቁ ትእዛዜንም ሁሉ ብትሽሩ ቃል ኪዳኔንም ብታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፡፡  ፍርሃትን ክሳትንም አይኖቻችሁንም የሚያፈዝዝ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፡፡ ዘሌ. 26÷4-16 ይላል እግዚአብሔር አምላክ

  እግዚአብሔርንም ከሀብትም ከክብርም ከሌላውም ሁሉ በፊት ጤንነቴን እና በሕይወት እንድኖር ዕድሜ ለንስሓ ስጠኝ ብሎ መለመን ትልቅ አስተዋይነት ነው፡፡ የማናቸውም ነገር ሁሉ ዋናው መሠረቱ ጤንነት ስለሆነ ጤንነት ካለ ሠርቶ ለመብላት ሀብት ለማግኘትና ለመክበር ሌላም ነገር ለማከናወን ይቻላል፡፡

  ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለተፈጠረ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ይፈልጋል መገናኛውም ጸሎት፣ ጾም፣ ስግደት፣ ምጽዋ በተለይ በመጪው ሰሙነ ሕማማት እና ንስሓ ነው፡፡

  እነ ሙሴ ሳሙኤል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ጸሎታቸውን ጽፈውልናል፡፡ የእኛ ጸሎታችን እንደሚከተለው መሆን አለበት፡፡

  1ኛ. በእምነት - ዕብ. 11÷6

  2ኛ. እደ እግዚአብሔር ፈቃድ 1ኛዮሐ. 5÷14

  3ኛ. በመንፈስ ቅዱስ  - ይሁ. 20÷

  4ኛ. ንስሐ በመግባት - መዝ. 66÷18

  5ኛ. ይቅር ባይ በመሆን - ማቴ. 6÷14

  6ኛ. ባለ መሰልቸት - ሉቃ. 11÷5

  7ኛ. በነገር ሁሉ - ፊል. 4÷6

  8ኛ. ስለ ሰው ሁሉ - 1ጢሞ. 2÷1

  9ኛ. በማንኛውም ጊዜ ሁሉ 1ኛተሰ. 5÷17 ናቸው ከኛ የሚጠበቀው፡፡

   

  አባ ሳሙኤል

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

  የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

  ሊቀ ጳጳስ

  facebookhttp://facebook.com/ EOTC.DICAC

  ‹ Back to List