Skip to main content

  "እንኳን ለ2012 ዓ.ም በዓለ ትንሣኤ በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ!!" ABGELAUFEN SEIT 16.04.2020

  17.04.2020
  "እንኳን ለ2012 ዓ.ም በዓለ ትንሣኤ በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ!!"

  ትንሣኤ ማለት ከሞተ ሥጋ በኋላ እንደገና እንደቀድሞው በሥጋ ለመኖር በሥጋ እና በነፍስ ተዋሕዶ መነሣት ማለት ነው::

   

          eotc1

  ትንሣኤ

  ቅዱስ ያሬድ፡      ትንሣኤከ ለእለ አመነ፡፡

                                ብርሃነከ ፈኑ ደቤነ፡፡

  ትርጉም፡- ትንሣኤህን ለምናምን ብርሃንህን ለእኛ ላክልን፡፡

  ዝማሬውን የዘመረው ኢትዮጵያዊ ሊቀ ቅዱስ ያሬድ ነው በዚህ የቅዱስ ያሬድ ምሥጋና ሦስት ነገሮችን እንመለከታለን፡-

  1ኛ/ ትንሣኤ

  2ኛ/ እምነት / ለእለ አመነ/

  3ኛ/ ብርሃን /ብርሃነከ ፊኑ ደቤነ

  1ኛ/ ትንሣኤ ማለት ከሞተ ሥጋ በኋላ እንደገና እንደቀድሞው በሥጋ ለመኖር በሥጋ እና በነፍስ ተዋሕዶ መነሣት ማለት ነው ይህን የመሰለ የፍጡራን ትንሣኤ ከሙታን መካከል ለይቶ የሚያስነሳ መለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ 1ኛ ትንሣኤ አልዓዘር

       ዮሐ 11፡43 ይህንም ብሎ በታላቅ ድምጽ እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ ወጣ ፊቱም በጨርቅ እንደተጠመጠመ ነበር ኢየሱስም ፍቱትና ይሄድ ተውት አላቸው፡፡

  2ኛ/ ትንሣኤ ወለተ ኢያኢሮስ፡- ማቴ 9፡23 ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ እምቢልተኞችንና የማንጫጫውን ሕዝብ አይቶ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው በጣምም ሳቁበት ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት ብላቴናይቱም ተነሣች፡፡

        እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው የእግዚአብሔር ሰዎች የመነሳታቸው ምክንያት የባህርይ አምላክ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የእርሱ ትንሣኤ ግን በብርሃን፣ በሥልጣን፣ በክብር እና በምልዓት የተከናወነው በራሱ በወልደ አምላክ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ነው፡፡ ለምን ቢሉ የባህርይ አምላክ የእግዚአብሔር አብ ልጅ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ነው፡፡

  መዝ፡ 77፡65      ወተንሥአ፡ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምንዋም፡፡

                    ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን፡፡

                    ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ፡፡

  ትርጉም፡- እግዚብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሳ፡፡

             የወይን ስካር እንደተወው ኃያልም ሰው ፡፡

             ጠላቶቹን አጋንንትን በኋላው መታ፡፡

  ይህ ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ለአዳም እና ለሔዋን ገነት መንግሥተ ሰማያትን  ይወርሱ ዘንድ ፈረደላቸው፡፡ በአጋንንት ፈረደባቸው ማለት ነፍስን በሲኦል ሥጋን በመቃብር ከመግዛት ሻራቸው፡፡ በኋላው በተተከለ መስቀል (በተሰቀለበት መስቀል) ታናሽ፣ ተከታይ ጠላት ዲያብሎስን ድል ነሣው ገደለው፡፡

  መዝ ዘቅ/ያሬድ፡- ተንሥአ ወአንሥአ ኵሎ ሙታነ ወፈትሖሙ ለመቁሐን፡፡ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፡፡ ወአግዓዘ ነፍሰ ጻድቃን፡፡ ለአልዓዛር ተንሥእ ዘይቤሎ፡፡ ወለዕውርኒ ዘፈወሶ በቃሉ ትንሣኤሁ ገብረ በሰንበት በሣልስት ዕለት ተንሥአ ወአንሥአ ኵሎ ሙታነ ወፈትሖሙ ለመቁሐን፡፡

  ትርጉም፡- ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብዙ ሙታንንም አስነሳ፡፡ በታለቅ ኃይልና ሥልጣን በሲኦል ጨለማ የታሰሩትን ፈታ፡፡ በሲኦል የነበሩትን ጻድቃንን የዓርስተ አበውን ነፍስ ነፃ አወጣ፡፡ አልዓዛርን ከሙታን መካከል ተነሥ ያለው ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን በቃሉ የፈወሰውን ትንሣኤውን በሰንበት በሦስተኛው ቀን አደረገ፡፡

  ከላይ የተመለከትናቸው የልበ አምላክ የቅዱስ ዳዊት ዝማሬ (ደረቅ ትንቢት) እና የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ የሚያስገነዝበን የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በባህርይ ክብሩና በመለኮታዊ ሥልጣኑ ለእኛ ድኅነት የተከናወነ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

  2ኛ/ እምነት (ለእለ አመነ) ለአመንን ለእኛ ለምዕመናን አንድ ሰው ለመዳን የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ ከሦስቱ አካላት አንዱ በተለየ ስሙ ወልድ በተለየ ግብሩ ተወላዲ የሆነ የእግዚአብሔር አብን የባህርይ ልጅ ሰው መሆን (ትስብዕት)፣ መጠመቅ፣ መከራ መቀበል፣ በፈቃዱ መሞት እና በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ መነሣት ማመን ያስፈልጋል፡፡ አንድን ሰው ክርስቲያን የክርስቶስ ተከታይ የሚያሰኘው ይህ መሠረታዊ እምነቱ ነው፡፡

  ሮሜ 6፡1-6 እንግዲህ ምን እንላለን ? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም፡፡ ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቀን አታውቅምን?  እንግዲህ ከክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡ ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤው ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፡፡

       እንግዲህ ይህን እምነት ዓለምማቀፋዊት፣ ሐዋርያዊት፣ አንዲት እና ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ዘወትር በምትሰዋው የወልደ አምላክ ሥጋወ ደሙ ላይ ለዓለም ስትመሰክር እስከ ምጽአት ድረስ ትኖራለች፡፡

  ቅ/ሐዋ 47 ንዜኑ ሞትከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ ነአምን ዕርገተከ ወዳግመ ምጽአተከ ንሴብሐከ ወንትአመነከ ንስእለከ ወናስተበቀዐከ ኦ.እግዚእነ ወአምላክነ

  ትርጉም፡ አቤቱ ሞትህን ቅድስት ትንሣኤህንም እንናገራለን (እናምናለን) ዕርገትህን ዳግመኛ ለፍርድ መምጣትህን እናምናለን እናመሰግናለን እናምንሃለንም ጌታችን እና አምላካችን ሆይ እንለምንሃለን እንማልድሃለንም፡፡

  3ኛ/ ብርሃን (ብርሃነከ ፊኑ ዲቤነ)፡፡ ሕይወት የሆነች የሰው ብርሃን መገኛ ከአንተ ዘንድ ነችና ከ5500 ዘመን በኋላ በፍቅርህ ብዛት ቤዛ ሆነህ ከግብርናተ ዲያብሎስ ወደ ልጅነት ክብርና ሥልጣን ከመንጸፈ ደይን ወደ ገነት መንግሥተ ሰማያት ርስት  የመለስከኝ ጌታዬ አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በትንሣኤህ ያጐናጸፍከኝን ብርሃን ላክልኝ፡፡ የእርሱ ብርሃንነት በመጀመሪያም በወንጌሉ ተመስክሮ ነበር፡፡ ዮሐ 1፡4 በእርሱ ሕይወት ነበረች ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች፡፡ ብርሃንም በጨለማ ይበራል ጨለማም አላሸነፈውም፡፡ በእርሱ ቃል የተነገረ ትንሣኤው በባለቤቱ በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈፀመው ትንሣኤው ለፍጥረቱ ሁሉ ከጨለማ ሲኦል የዳነበት የሕይወት ብርሃን ነው፡፡

  ዮሐ 1፡9 ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡ በዓለም ነበረ ዓለሙም በእርሱ ሆነ ዓለሙም አላወቀውም፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ የተገለጠው ይልቁንም ላመኑት ሕይወት መድኃኒት የሆነው ጨለማን ያራቀ የሕይወት ትንሣኤ ብርሃን ያጎናጸፈን ጌታ እግዚአብሔርን ድኅነታችን፣ ደስታችን እና ተስፋችን ነው፡፡

  ቅ/ ያዕ 83፡ ኦ ገባሬ ብርሃናት ዘደፍኦ ለጽልመት ወሠዐሮ ለጣኦት ዘበሞቱ ደምሰሶ ለሞት፡፡

  ትርጉም፡ የብርሃናት ፈጣሪ ሆኖ ጨለማን የደፋው ጣኦትንም የሻረው በሞቱ ሞትን ያጠፋው፡፡

  ቅ/ያሬድ መወድስ፡-     እምዕቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ

                          ብርሃናተ ዘይትአፀፍ ተንሥአ ለነ፡፡

  ትርጉም፡-   ከሚነድ የእቶን እሳት አዳነን፡፡

                    ብርሃንን የሚጐናጸፈው ተነሳልን

  የሰው ልጆች ከአጋንንት እስራት ከሲኦል ጨለማ ከሃነመ እሳት የዳኑበት የወልደ እግዚአብሔር ከሙታን ተለይቶ መነሳት ለአይሆድ እፍረት ለአጋንንት ሽንፈት (ድል መነሳት) ሲሆን ለምዕመናን ክርስቶስ የዘለዓለም ዕረፍትና ሕይወት ነው፡፡ አይሁድም ይህ ሀፍረት እንዳይደርስባቸው ፈርተው የጌታን መቃብር በወታደሮች አስጠብቀው ነበር

  ማቴ 27፡62 የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና ጌታ ሆይ ያ አሳች በሕይወት ገና ሳለ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን፡፡ እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛየቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩን እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት፡፡ በሰው ልጅ የድኅነት ጉዞ ከድንግል ማርያም መወለድ ጀምሮ እስከ ስቅለቱ ያልተለየው የሰይጣንና ፈተና ሥግው ቃል ጌታ እግዚአብሔር በማሸነፍ ከትንሣኤው ደርሷል፡፡

  ማቴ 2፡1-19፣ ማቴ 27፡ 1-50

  እንግዲህ የጌታችን ትንሣኤ ምንም ዓይነት የፍጡር ኃይል ሊከለክለው ስለማይችል አምላካችን በሥልጣኑ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ድንጋይ ፈንቅሉልኝ ሣይል በሥልጣኑ ከሙታን መካከል ተነሣ ዮሐ 20፡ 1-18፡፡ ቀድሞ በዘመነ ሥጋዌው ሥርዓትን እየሠራ ወንጌልን እያስተማረ በነበረበት ጊዜ ትንሣኤና ሕይወት እርሱ እንደሆነ በግልጽ የነገረን አምላክ ለእኛ ትንሣኤ በኵር ሆኖ ብርሃን ተጎናጽፎ ተነሣልን ዮሐ 11፡25፡፡

  በዚህ በጌታችን ትንሣኤ ይቅርታ፣ ድኅነት የተደረገለት የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የተደሰተው ሰማይ እና ምድር ሁሉም ፍጥረት ነው የተደሰተው፡፡ ዲያብሎስና ሠራዊቱ ግን ለዘለዓለም ነፍስን በሲኦል ሥጋን በመቃብር ከመግዛት ሥልጣን የተሻሩበት በመሆኑ ያዝናሉ ይህንንም ኢትዮጵያዊ ሉቅ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ በማለት ዘምሯል

  ቅ/ያሬድ፡- ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሠይ ምድር

  ትርጉም፡-   ሰማይ ይደሰታል ምድርም ሀሴት ታደርጋለች

                     ወዮምሰ ዓባይ ፍስሐ በሰማያት ወምድርኒ ትገብር

                     ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ

  ትርጉም፡- ዛሬስ በጌታ ትንሣኤ ታላቅ ደስታ በሰማያት ሆነ፡፡

  ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ (ነጽታ) ፋሲካን ታደርግለች ( ታከብራለች)፡፡

  ሁላችሁም የተወደዳችሁ የእግዚብሔር ልጆች ምዕመናን እንኳን ለ 2012 ዓ/ም በዓለ ትንሣኤ አደረሳችሁ ይህን የክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በመተሳሰብ፣ በመፈቃቀር፣ ምንም ለሌላቸው ወገኖች በማሰብ በመንፈሣዊ ክንዋኔ ልናከብረው ይገባናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በሥጋ ሥርዓት በስካር፣ በዘፈን፣ በጭፈራ እና በዝሙት ሥጋችንን እና ነፍሳችንን በኃጢአት በማርከስ አምላካችን እስከ ትንሣኤ ድረስ የከፈለልንን የድኀነት ካሣ በመዘንጋት መሆን የለበትም

  የተከበራችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች በሕይወት ስንኖር ነውና ትንሣኤን የምናከብረው በዚህ ዓመት በሀገራችንና በዓለም የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመከላከል ከቤተክርስቲያኗ እና ከሚመለከታቸው አካላት በተላለፈው መመሪያ መሠረት ሁሉም ሰው ርቀቱን ጠብቆ እና በቤቱ ሆኖ በዓሉን እንዲያከብር መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ በተለይም በቤተሰብም ሆነ ከጎረቤት ጋርም አለመሰባሰብ ይመረጣል፡፡

   እግዚብሔር አምላክ ከታዘዘው መቅሰፍት ሁሉ ይጠብቀን መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት ይመልስልን፡፡ በዓሉን በዓለ ፍስሐ ወሐሴት ያድርግልን ሀገራችንን ኢትዮጵያንና አለምን ሰላም ያድርግልን አሜን፡፡

   

  መልካም ትንሣኤ!!

  አባ ሳሙኤል

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተ/ቤ ክርስትያን

  የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

  ሊቀጳጳስ

   

  ‹ Back to List