Skip to main content

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲየናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ በጎ አገልግሎት የቆመ ክርስቲያናዊ ድርጅት (Christian Organization For International Voluntary Service-CVM) ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ መልእክት ABGELAUFEN SEIT 22.06.2020

  23.06.2020 Top news Media info
  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲየናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ በጎ አገልግሎት የቆመ ክርስቲያናዊ ድርጅት (Christian Organization For International Voluntary Service-CVM) ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ መልእክት

  "በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚሐብኤር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ" ፊሊጵ 4፡4

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን፡፡

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲየናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ በጎ አገልግሎት የቆመ ክርስቲያናዊ ድርጅት (Christian Organization For International Voluntary Service-CVM) ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ተግባር የልማት ኮሚሽናችን አስተዋጽኦ ለማድረግ የተዘጋጀ መልእክት

  በዓለማችን በተለያዩ ወቅታት የሰው ሕይወትን የሚቀጥፉ ወረርሽኝ ተከስተዋል፡፡ በዘመናችን የተከሰተው እና ዓለምን በአንድ ቋንቋ እያነጋገረ ያለው ዓለምአቀፍ ይዘት ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የዓለም መንግስታት እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም  በጤና ሚኒስቴርና በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አማካኝነት ስለበሽታው ስርጭት በየቀኑ ለህብረተሰቡ እያሳወቁ እና የበሽታውን መከላከያ ዘዴዎች ግንዛቤ እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

  ቤተክርስቲያናችንም ሃይማኖታዊ ግዴታዋን ለመወጣት ተከታይ ምእመኖቿንና ሌሎችንም የማኅበረሰብ አካላት በበሽታው እንዳይጠቁ ለመከላከል በቤተክርስቲያኗ እና በሌሎች ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በቤተክርስቲያን አገልግሎት፣ ሌሎችንም የማኅበረሰብ አካላት በኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት እና መንግስት በሚያዘጋጇቸው መድረኮች የጥንቃቄ መልእክቶችን ስታስተላልፍ ቆይታለች ፡፡

  ኮሚሽናችን የቤተክርስቲያኗ የልማት ክንፍ እንደመሆኑ ከዓለም አቀፍና አገር አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሀገሪቱ በሚተገበሩት የልማት ፕሮጀክቶች የኮቪድ-19 መከላከል ሥራዎችን በማካተት እየተገበረ ይገኛል፡፡

   

  እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ የኮሮና በሽታን ስርጭት ለመከላከል ምን መደረግ እንዳለበት በመጠኑ እንነጋገራለን፡-

  1.አብዝቶ መጠንቀቅ እንጅ አለመጨናነቅ - እመን ግን ተጠንቀቅ እንደተባለው

  "በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚሐብኤር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ"

   ፊሊጵ 4፡4

  • በበሽታው  የተነሳ  ጭንቀት እና ፍርሃት ቢሰማችሁም መደናገጥ አያስፈልግም፡፡ ማንም ሰው ሊሰማው የሚችል ስሜት ሊሰማን ይችል ይሆናል፡፡
  • በሽታው ከምድራችን እስኪወገድ ድረስ አኗኗራችንን ከምክረ ንስሐ አባቶቻችን፣ ከሃይማኖት አባቶች እና መምህራን ጋር በግልፅ መወያየት፡፡ ቤተሰቦቻችንንና ልጆቻችንን ማረጋጋት፡፡
  • በሽታውን ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለብን የጤና ባለሙያዎች የሚነግሩንን ምክር ተግባር ላይ ማዋል፡፡
  • ትክክለኛ መረጃ የሚሰጡ መገናኛ ብዙሃንንና ማህበራዊ ትስስሮችን መከታተል፡፡
  • ቤተክርስቲያን ውስጥና አውደምሕረት በምንገባበት ወቅት ርቀታችንን መጠበቅ፣ ክርስትና በማስነሳት፣ እና የነፍሳተ ሙታን መታሰቢያ ለማዘከር ቤተክርስቲያናት በሚፈቅደው መሠረት የሰው ብዛት ብቻ ተጠቅመን አገልግሎቱን ማግኘት፣
  • ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ የጸሎት ስርዓቶችን በቤተክርስቲያን ርቀታቸችንን ጠብቀን በቤታችን ውስጥ ደግሞ ከቤተሰቦቻችን ጋር መከወን ይገባል፡፡

  2. ራሳችንን እና ሌሎችንም ከበሽታው ለመጠበቅ የምናደርጋቸው ጥንቃቄዎች በጣም ቀላል ናቸው፡-

  • ጨለማው እስኪገፈፍ ድረስ  በቤተክርስቲያን ቢሆን የሰዎች መጨናነቅ ባለበት ቦታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፡፡
  • እግዚአብሔር የተሻለ ጊዜ እስኪያመጣልን ድረስ  በተለይ የተቸገሩትን ወገኖች በመርዳት፤ እርስ በእርስ በመተጋገዝ  ማኅበራዊ ግዴታችንን መወጣት ይገባል፡፡
  • የሰዎችን መሰባሰብ በሚፈልጉ ማህበራዊ ጉዳዮች (እንደ እድርና ማህበር) ማከናወን ግዴታ ከሆነ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም፣ ስታስነጥሱም ሆነ ስታስሉ አፋችሁን እና አፍንጫችሁን እጃችሁን በማጠፍ በክርናችሁ መሸፈን፤
  • እጆቻችንን ቶሎ ቶሎ እና በአግባቡ በሳሙና ቢያንስ ለ20 ሰኮንዶች መታጠብ፡፡
  • ባልታጠቡ ጣቶች ፊታችንን፣ አይኖቻችንን፣ አፍና አፍንጫችንን አለመነካካት፤
  • ቢቻል የመመገቢያ እቃወችን መለየት፣ ድንገት ከተዋስን እነኳ በውሃና ሳሙና በደንብ ማጠብ አለብን፡፡

       

                  corona

  Figure 1፡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ስንጠቀም ማድረግ የሚገባን ጥንቃቄዎች

  1.  ያወቅነውን ለሌሎች እናሳውቅ
  • ወረርሽኙን ለመከላከል ማንም ሰው ያወቀውን በሙሉ ለቤተሰቡ፣ ለጓደኞቹና ለህጻናትም ማስተማር አለበት፡፡
  • ሁላችንም ባገኘነው ሁሉ አጋጣሚ በቤታችንና በሥራ ቦታዎች ያወቅነውን በማሳዎቅ፣ በተግባር በማሳየት አርአያ ልንሆን ይገባል፡፡

       2. የበሽታው ምልክት የታየባቸውን፣ የታመሙትንና ከለይቶ ማቆያ የወጡትን ሰዎች አለማግለልል፡፡

  • ከለይቶ ማቆያ ወይንም ከሆስፒታል አገግሞ የወጣን ሰው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ማግለል፣ወይም በበሽተኞች ላይ ማፌዝ እግዚአብሔርንም  ሰውንም ማሳዘን ነውና ከዚህ ተግባር እንቆጠብ፡፡
  •  ሆኖም ግን በሽታው በንክኪ፣ በማስነጠስ እና በሳል ስለሚተላለፍ በዚህ በሽታ የተጠረጠረ ወይም መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ርቀታችንን መጠበቅ መዘንጋት የለብንም
  •  ነግ በእኔ ነውና የተቸገሩትን ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ዘርና ጎሳ ሳንለይ ለመርዳት መነሳት ይኖርብናል፡፡  

       3.  አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር በቤት ውስጥ መቆየት የመጀመሪያ አማራጫችን መሆን ይገባዋል፡፡

    

  በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተገለጸው፡-

  መጽሐፈ መክብብ ምራፍ 3፤1-6 ለሁሉ ዘመን አለው፡- ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው የሚለውን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

  የበሽታው ምልክት ከታየባችሁ ከቤት ሳትወጡ ባስቸኳይ የህክምና እርዳታ ጠይቁ!

  "ሕዝቤ ሆይ ና ወደ ቤትህም ግባ ደጅህን ወደኋላህ ዝጋ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ፡፡"ኢሳ፡ 20፡- 26

  ስለዚህ ይህ ክፉ ቀን  እስኪያልፍ ድረስ በቤት መቆየት ተገቢ ነው፡፡

  እንደ ጉንፋን የቀለለ የሚመስል ወይም ማናቸውም የህመም ስሜት ከተሰማችሁ ከቤታችሁ አትውጡ፡፡ አልጆቻችሁንም ከቤት ከመውጣት ከልክሉ፡፡

   

  corona 1

  Figure 2: እጅ ስንታጠብ መከተል የሚገባን ቅደም ተከተሎች

   

  በቤት ውስጥ ስንቆይ፡-

  • ከቤተሰቦቻችን፣ ከጎረቤቶቻን ጋር በሰላምና በጥሩ ስነምግባር መቆየት ይገባናል!!
  • ትምህርታቸውን በቤት ውስጥ እየተከታተሉ ለሚገኙት ህጻናት ልጆቻችንን ማስጠናት፣ ጊዜ ሰጥተን አእምሯቸውን ዘና የሚያደርግ ለእድሜአቸው ተስማሚ የሆኑ ታሪኮችንና፣ ተረቶችን ማንበብ፤ ወይም እንዲያነቡ ማበረታት፣ መዝሙሮችን እንዲሁም ጨዋታ እንዲጫወቱ በጨዋታዎች በንቃት እንዲሳተፉ ማገዝ፡፡ 

   

  በአንዳንድ ሰዎች በስነምግባር ችግር ምክንያት በአሁኑ ወቅት የቤት ውስጥ የሴቶች ህፃናት ጥቃት እንዲሁም የወንድ ሕጻናት ጥቃት እየተበራከተ ስለመጣ ወላጆች፣ የሚመለከታቸው የመንግሥትና ማኅበረሰብ አካላት ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማድረጋቸውን መቀጠል ይገባል፡፡

   

     በመጨረሻም፡-

  •   ከባለሙያተኞች የሚሰጠንን ምክር እንስማ፡፡
  •   አበው እና ጠቢባኑ የሚሰጡትን ምክርሰምተን እንተግብር!
  •   አምላክችን እግዚአብሔር ለሀገራችን ብሎም ለዓለማችን ሰላምን ለሕሙማን ፈውስን ያድልልን!
  •   አምላካችን እግዚአብሔር ሕዝባችንን ከሞት፣ ሀገራችንንከጥፋትይሰውርልን!
  •   በዓለማችን የተከሰተውን ወረርሽኝ ያርቅልን ዘንድ የስጋም የነፍስም መድኃኒት ወደ ሆነው አምላካችን በጸሎትና በምህላ እንትጋ፡፡ 

  አባ ሳሙኤል

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

  ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

    logo 1                                               download

                             
   https://www.facebook.com/EOTC.DICAC
   

   

  ‹ Back to List