Skip to main content

የነፍስ ሞት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡

11.04.2020 Media info Top news
የነፍስ ሞት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡

ሕመም የሥጋም የነፍስም መከራ ነው፡፡ ነፍስ በተፈጥሮዋ መንፈስ በመሆኗ እንዴት ልትታመም ትችላለች? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ነፍስ እንደ ሥጋ ያለ ሕመም፣ ድካም ረኃብ ወይመ ጥም ወዘተ ባይኖርባትም መንፈሳዊ ረኃብ ጥም ሕመም እንዲሁም ሞት አለባት፡፡

የነፍስ ረኃብ ቃለ እግዚአብሔር ከመስማት መራቅ ነው፡፡ ዳግመኛም የክርስቲያን ነፍስ ረኃብና ጥሟ ከሥጋ ወደሙ መለየት ነው፡፡ የነፍስ ሕመም (ደዌ) ጭንቀትና ሁከት ነው፡፡ “አሁን ነፍሴ ታወከች ምንስ እላለሁ?” ዮሐ. 12÷27፡፡ የነፍስ ሞት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ “ሞታ ለነፍስ ርኂቅ እግዚአብሔር የነፍስ ሞት ከእግዚአብሔር መራቅ (መለየት) ነው፡፡” ዳግመኛም ነፍስና ሥጋ እንደ ብረትና እሳት የተዋሐዱ በመሆናቸው የሥጋ መከራ ሁሉ የነፍስም እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ አንድ ሰውን ሰው የሚያሰኙት የሥጋና የነፍስ ውሕደት ነው፡፡ ነፍስ የሌለው ሥጋ ሰው አይባልም፡፡ ሥጋም የሌላት ነፍስም እንዲሁ፡፡ ያዕ. 2÷26

ሕመም አራቱን የሥጋ ባሕርያት እንዲጋጩ (ተቃርኖ እንዲፈጥሩ) የሚያደርግ ወይም አንዱ ባሕርይ በሌላው ላይ እንዲሰለጥንበት በማድረግ ሰዎችን ለመከራ የሚዳርግ ነው፡፡ ሰው ሲታመም የሚያተኩሰው ከሆነ የእሳት ባሕርይ በርትቷል፡፡ ብርድ ርድ የሚል ከሆነ የነፋስ ባሕርይ፣ የሚያልበት ከሆነ ደግሞ የውኃ ባሕርይ አይሎ ነው፡፡ በሕመም የተያዘ ሰውነት መንፈሳዊ ተግባሩን ማከናወን አይችልም፡፡ የሚያዳምጠው የሕመሙን ንዝንዝና ጥዝጣዜ ነውና፡፡ ሕመም ዝንጉዎችና ግብዞችን ከእግዚአብሔር ሊያርቃቸውም ይችላል፡፡ ያማርራሉ እንጂ ተመስገን አይሉምና፡፡ መከራ ግብዞችን ከእግዚአብሔር እንደሚያርቃቸው ይነግረናል፡፡

በኃጢአት ምክንያት የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከወሰደ ድረስ እንዳላወቁ ሁሉ በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፣ አንዱ ይወሰዳል አንዱ ይቀራል፣ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፣ አንዲቱ ትወስዳለች አንዲቱ ትቀራለች፡፡ ማቴ. 24÷39 በዘመናችን እያየን ያለነው ይህ ነው እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ፡፡

ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡

ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ነገር ግን ሸሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፡፡

ችግር ፈጣሪ ሰው ራሱ ነው፡፡

መራብና መጠማትን፣ መታመምና መሞትን ይህንና የመሳሰለውን ችግር ስቦ ጐትቶ ከሩቅ ተጣርቶ የዛፉን ፍሬ አሁንም በድጋሚ ሕገ እግዚአብሔርን ጥሶ በለሱን በልቶ ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ የሰው ልጅ ወዶ ለምዶ በገዛ ፈቃዱ ያመጣው የሕይወቱ መዘዝ ነው፡፡ የሚከተሉትን መረጃዎች ከቅዱስ መጽሐፍ እንመልከት፡፡

  • ሤምኩ ቅድሜከ ሕይወተ ወሞተ መርገመ ወበረከተ ኅረይ ለከ ለሕይወት ከመ ትሕየው አንተ ወዘርዕከ እምድኅሬከ

ትርጉም፡- ሕይወትና ሞትን መርገምንና በረከትን በፊትህ አኖርሁ ነገር ግን አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ ይላል የእግዚአብሔር ቃል ዘዳ. 30÷15፣ ዘዳ. 30÷19

  • አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ ደይ እዴከ ኀበ ዘፈቀድከ

ትርጉም፡- እሳትንና ውኃን በፊትህ አቀረብሁልህ እጅህን ወደፈለግኸው ጨምር፡፡ ሕይወትና ሞት በሰው ፊት ናቸው፡፡ ከእነርሱም የመረጡትን ይሰጡታል በማለት ረሃብንና ሞትን የሰው ልጅ በነጻ ፈቃዱ ያመጣቸው እንደሆኑ ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ሲራክ 15÷15

  •  እግዚአብሔርሰ ኢገብረ ሞተ አላ ረሲዓን ሰብእ ጸውእዎ በቃሎሙ ወአርከ አምሰልዎ፡፡

ትርጉም፡- እግዚአብሔርስ ሞትን አልፈጠረም፡፡ ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች በእጃቸው እንመራመራለን ብለው ሞትን ጠሩት ወዳጅም አደረጉት እንጂ መጽ. ጥበብ 1÷18

  • ኃጢአትሰ ኢተፈነወት ዲበ ምድር አላ ሰብእ እምርእሶሙ ፈጠርዋ ወለመርገም ዐቢይ ይከውኑ እለ ገብርዋ ኃጢአተ ፡፡ ከሰማይ ወደምድር አልተላከችም ሰዎች ራሳቸው ፈጠሯት እንጂ ኃጢአትን  የሠሯትም ሰዎች በጽኑ ፍዳ ይያዛሉ መጽ.ሄኖክ፡፡

በመጻሕፍተ ብሉያት ከላይ የተዘረዘሩትን መረጃዎች መሠረት በማድረግ አሞንዮስና አውሳብዮስ የተባሉ ቅዱሳን ሊቃውንትም በመቅድመ ወንጌል ማብራሪያቸው ላይ ስለሰው ልጆች የነጻነት መብት እንዲህ በማለት ገልጸውታል፡፡

  • "ወገብረ ላቲ ሥልጣነ ትግበር ዘከመ ኀርየት እንዘ አልቦ ዘይኴንና ወዘይኄይላ"

ትርጉም፡- የሰዎች ልቡና ወይም ለባዊት ነባቢትና ሕያዊት ነፍሳቸው የሚሰለጥንባትና የሚያስገድዳት ሳይኖር የወደደችውን እንደ ወደደች ታደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ሙሉ ሥልጣን ነጻ መብት ሰጣት በማለት የሰው ልጅ መልካም ሥራ ሠርቶ እንደሚጠቀም ክፉ ሥራም ሠርቶ እንደሚጐዳ የሚያውቅበትን አእምሮ ልቡና ሰጥቶ ፈጣሪ ዓለማት ጌታ እንደፈጠረው ሊቃውንቱ መስክረዋል፡፡ መቅድመ ወንጌል

ስለሆነም ረሀብና ቸነፈር በሽታና ሞት ድርቅና ጦርነት የሚመጣው በመሬት ጥበት በሕዝብ ብዛት ሳይሆን ከላይ እንደተጠቀሰው የሰው ልጅ መልካም ይሁን ክፉ ሥራ የመሥራት ነጻ መብቱን ተጠቅሞ ፈጣሬ ፍጥረታት መጋቤ ዓለማት እግዚአብሔርን ባለማወቁ እና ለሕገ እግዚአብሔር ተገዢ ባለመሆኑ ብቻ ነው፡፡   

  • “ወኲሎ ኅሊናክሙ ግድፉ ላዕሌሁ እስመ ውእቱ ይኄሊ በእንቲአክሙ”

ትርጉም፡- ሐሳባችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት ወዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ ሳንለምነው የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል የተባለው ለጋሱ አባት ስለ እናንተ ያስባልና በማለት ሐዋርያው የጌታን መጋቢነት መስክሯል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም “ውእቱ ይሁብ ዘርዓ ለዘራኢ ወእክለ ለሲሳይ” እርሱ ጌታ ለሚዘራ ዘሩን ለሚመገብ ለተራበ ምግቡን ይሰጠዋል በማለት ዘምሯል፡፡

ድርቅና ቸነፈር በሽታና ሞት ርሃብና ጦርነት በሕዝብ ብዛት በመሬት ጥበት በሥነ ተፈጥሮ መዛባት የሚመጣ ካልሆነ ችግሩን ከነመፍትሔው ስለሚያስረዳን ዓለም አቀፉ ሕዝበ ክርስቲያን የሚቀበለውን ታላቁን ቅዱስ መጽሐፍ እስኪ ሰፋ አድርገን እንመልከተው፡፡

  •  “ወለእመ ሰሚዐ ሰማዕከ ቃለ እግዚአብሔር አምላክከ ወአቀብከ ትዕዛዞ ይሬስየከ እግዚአብሔር መልዕልተ ኩሉ አሕዛበ ምድር ወይበጽሐከ ዝንቱ ኩሉ በረከት”

ትርጉም፡- የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ ሕጉንም ብትጠብቅ ከአሕዛብ ሁሉ በላይ ያደርግሃል፡፡ ይህ ሁሉ በረከት (ምርቃት) ይደረግልሃል በከተማም በበረሃም በገጠርም የተባረክህ ትሆናለህ፡፡ ከአብራክህ የተከፈለ ልጅህም የተመረቀ ይሆናል፡፡ የምድርህ አዝመራም የበረከተ ይሆናል የበጐችህና የላሞችህ መንጋ የተባረከ (የበረከተ የበዛ) ይሆናል፡፡ ድልብህና ገንዘብህም ማለትም አዲሱ አዝመራህና የከረመው እህልህ ሁሉ የበረከተ ይሆናል፡፡ ኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 28፡- 1-14 ይመልከቱ

  • “ወይፈትሕ ለከ እግዚአብሔር መዝገበ ቡሩከ ሰማይ ከመ የሀብከ ዝናመ በመዋዕሊሁ ከመ ይባርክ ለከ ኩሎ ተግባረ እደዊከ፡፡”

ትርጉም፡- እግዚአብሔር ለምድርህ በየወቅቱ (በየወራቱ) ዝናምን ይሰጥህ ዘንድ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል ማለት ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ይሰጥሃል በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ዘዳ. 28÷12 ሰዎች በሕገ እግዚአብሔር ከተመሩ ዝናመ ምሕረቱ ጠለ በረከቱ ወቅቱን እየጠበቀ ይቀርብላቸዋል፡፡ የምድርንም በረከት ይጠግባሉ በዚህ ጊዜ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናም ይመጣል፤ አይመጣም የሚል የሜትሮሎጂ አገልግሎትም መረጃ አያስፈልጋቸውም፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ሰዎች ሕገ እግዚአብሔርን ካልጠበቁ በሕገ እግዚአብሔር ካልተመሩ ግን ከላይ የተጠቀሰው በረከት እንደማይገኝ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል

  • ወለእመ ኢሰማዕከ ቃለ እግዚአብሔር አምላክከ ይከውን ሰማይ በመልዕልተ ርእስከ ብርተ ወምድርኒ በታሕቴከ ሐጺነ

ትርጉም፡- የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ቃል ካልሰማህ ሕጉንም ካልጠበቅህ  ሰማይ እንደ ብረት የደረቀ ይሆናል፤ ምድርም እንደ ናስ ይሆናል፡፡ ዘዳ. 28÷24 ማለት ሕገ እግዚአብሔርን ካልጠበቅህ ሰማይ ዝናም ለዘር ጣል ለመከር አይሰጥህም ምድርም የዘራህባትን አታበቅልም የተከልህባትን አታጸድቅም እንዲህ ከሆነ ዝናም ከሌለ የሰው ልጅ ሆይ ምኑን ትበላለህ? ምኑን ትጠጣለህ? ወንዙና የከርሠ ምድሩም ውኃ እኮ ዝናም ከሌለ ይደርቃል፡፡ ባሕሩም እኮ ያልቃል፡፡

ስለዚህ ሰው ሆይ ሕይወትህ በሙሉ በእግዚአብሔር እጅ የተያዘ ነውና ከሕገ እግዚአብሔር ፈቀቅ አትበል ይላል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መልእክት በተጨማሪም ሕገ እግዚአብሔርን በመጠበቅ ትእዛዙንም በመፈጸም ሕይወትና በረከት ዝናመ ምሕረት ጠለ በረከት እንደሚገኝ ከኦሪት ዘሌዋውያንም ላይ እንዲህ እናነባለን፡፡ ዕቀቡ ሰንበታትየ ወፍርሁ እምቅዱሳንየ ወለእመ ሖርክሙ በትዕዛዝየ ወዐቀብክሙ ኩነኔየ እሁበክሙ ዝናመ በጊዜሁ ወምድርኒ ትሁብ እክለ ወእፀወ ገዳምኒ ይሁቡ ፍሬሆሙ

ትርጉም፡- ሰንበታትን አክብሩ ቅዱሳንን (ነቢያት ካህናትንም ፍሩ ማለት አክብሩአቸው በትዕዛዜ ጸንታችሁ ብትኖሩ ሕጌንም ብታከብሩ የበልጉንና የመከሩን ዝናም እሰጣችኋለሁ፡፡ ምድርም የዘራችሁባትን ታበቅላለች የተከላችሁባትን ታጸድቃለች፡፡ የምድረ በዳ እፀዋትም አዝርዕቱ አትክሉቱም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ፡፡ (በረከታቸውን ይለግሳሉ) ይላል ፈጣሬ ዓለማት መጋቤ ዓለማት እግዚአብሔር አምላክ፡፡ ኦሪት ዘሌ. 26÷2-4

  • “ወእመሰ እስከ ዝንቱ ኢፈራህክሙኒ አላ ሖርክሙ ግድመ ምስሌየ በኃጢአት ወአነኒ አሐውር ግድመ ምስሌክሙ በመዓት ወእትቤቀለ ክሙ ምስብዒተ በእንተ ኃጢአትክሙ”

ትርጉም፡- እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ አግድማችሁ በኃጢአት ብትሔዱ ግን እኔ ደግሞ በቁጣ (በፍርዴ) አግድሜ እሄድባችኋለሁ፡፡ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እበቀላችኋለሁ፡፡ ሰይፍ ጦርነት ቸነፈር ረሃብ ደዌ አመጣባችኋለሁ ይላል፡፡ ዘሌ. 26÷23 እስከፍጻሜ በአንጻሩ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ባይሰማ ሕጉንም ባይጠብቅ ግን ከላይ የተጠቀሰው በረከት ሳይሆን በተቃራኒው እንደሚደረግበት በረከቱ በመርገም ብልጽግናው በድህነት እንደሚለወጥበት ከኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 28 ከቁጥር 15 ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ብንመለከት ልንረዳ እንችላለን፡፡ ኦሪት ዘኁል. 28÷15-30

“መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” ዘካ. 1÷3፣ ማቴ. 3÷1

ዓለማችን በኃጢአት ደዌ ተይዞ በራሱ በአመጽና ሕገ እግዚአብሔር ሕግ በመተላለፍ ሞትና ደዌ ጠርቶ አምጥቶታል በዚሁም ያልበለጸጉና የበጸጉ በደዌ እየተመቱ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ለኃጢአታችን በደላችን ይቅር ይለን ዘንድ ንስሓ አስፈላጊ ነው፡ ማቴ 8÷4 - 16÷19 ወደ እግዚአብሔር መመለስ ከኃጢአት መንጻት ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ ሁሉን የሚያውቅ ማዕምረ ኀቡአት እግዚአብሔር በደላችንን ይቅር ይለን ዘንድ በንስሓ ያደረግነውን በመጸጸት መመለስ ከኃጢአት መንጻት ያስፈልጋል፡፡ እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥተ ሰማይን ትወርሱ ዘንድ ወደ እኔ ኑ፡፡ ብራብ አብልታችሁኛልና

ብጠማ አጠጥታችሁኛልና

እንግዳ ብሆን ተቀብላችሁኛልና

ብታመም ጐብኝታችሁኛልና

ብታሠር መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና

ብታረዝ አልብሳችሁኛልና እንዲለን

እግዚአብሔር አምላክ ሕጉን ለመፈጸም ያብቃን፡፡

 

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

ሊቀ ጳጳስ

              facebook    http://facebook.com/ EOTC-DICAC

‹ Back to List