Skip to main content

“እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቀችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” 1ኛ. ጴጥ 5፡ 7

15.04.2020 Media info Top news
“እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቀችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” 1ኛ. ጴጥ 5፡ 7

ጥበብ መንፈሳዊውን ከጥበብ ሥጋዊ ጋር አንድ አድርገው በያዙ ሰዎች ሀገር ትጸናለች፡፡ ይኸውም ጥበብ መንፈሳዊ ማለት የሚያምን፤ የሚታመን፤ በእምነቱ ጽኑ ተስፋ ያለው አማኒ፤ እሙን፤ የማይጠራጠር በነቢያት ትንቢት የተነገረውን የእግዚአብሔርን ህሉና የተረዳና ያወቀ አማኝ አይጨነቅም፡፡ ማለትም፡-

 • “የእስራኤል ቅዱስ ሰሪውም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ ምድርን እኔ ሰርቻለሁ፤ ሰውንም በእርሷ ፈጥሬያለሁ፤ ሰማያትን በእጀ ዘርግቻለሁ፤ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ ይላል፡፡” ኢሳ. 45፥ 11-12፡፡
 • “የፈጠረን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡  እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፤ እረዳህማለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ፡፡” ኢሳ. 41፡ 10
 • “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ ርሱን ዕወቅ ርሱም ጎዳናህን ያቀናል፡፡”  ምሳሌ. 3፡ 5-6
 • “በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ”  ኢሳ. 26፡3
 • “አምላካችን መጠጊያችን ኃይላችን፤ ባገኘን በታላቅ መከራም ጊዜ ረዳታችን ነው፡፡ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራራዎችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ፤ አንፈራም ውሃወቻቸው ጮሁ ተናወጡም ተራራዎችም ከኀይሉ ጽናት የተነሣ ተናወጡ፡፡” መዝ.45 (46) 1-3፡፡

 

 • “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ ርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል፡፡” 

          ምሳሌ 3፡- 5-6

 •  በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት “ሰላሜን እተውላችኃለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም፡፡ ልባችሁ አይታወክ አይፍራም፡፡” ዮሐ. 14፡7፡፡

 

 • “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬያችኋለሁ፡፡ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁና፡፡”  ዮሐ. 16፡33፡፡ 
 • በሐዋርያት ስብከት፡-  “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና”  2ኛጢሞ 1፡7፡፡

በመሆኑም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረትነት፤ በሊቃውንት ትምህርት ጸንቶ የኖረ፤ ለፈጣሪ ለእግዚአብሔር በጾም በጸሎት በስግደት በልዩ ልዩ ትሩፋት የበለጸገ፤ ጸዋሚ ተሐራሚ ሆኖ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥና የሥጋን ሞት የማይፈራ፤ የእግዚአብሔር ሀልዎቱን፤ አንድነቱን፤ ሦስትነቱን፤ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ የሠራውን የአድኅኖት ሥራውን፤ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መሆኗንና አማላጅነቷን የተሰጣትንም የአማላጅነት ቃል ኪዳን የሚያምን፤የቅዱሳን ነቢያትን፤ የቅዱሳን ሐዋርያትን፤ የቅዱሳን ጻድቃንን፤ የቅዱሳን ሰማዕታትን ክብርና የተጋድሎ ቃል ኪዳን አማላጅነትና ተራዳኢነት፤የጾምንና የጸሎትን ጠቃሚነትና አስፈላጊነት አምኖ የሚተገብር ነው፡፡

በተለይም ነቢየ እግዚአብሔር ልበ አምላክ ቅዱስ በመዝሙሩ እንደ ነገረን፡-

 • “ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቀኝ መልካም ሆነልኝ፡፡” መዝ.118 (119)፡ 71 ያለውን ቃል መሠረት በማድረግ ልንበረታና ልንጸና እንጂ ልንጨነቅ እንደማይገባን አስተምሮናል፡፡
 •  ይልቅስ፡-  “በተጨነቅሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ ሰማኝም”  119 (120) ፡1 በሚለው ቃል መሠረት ፈጣሪያችን ልንማጸነውና ልንለምነው እንዲሁም እንደ ነቢዩ:- ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ፤ እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ ሕያውም እሆናለሁ ከተስፋዬም አልፈር ማለት ይገባናል እንጂ መጨነቅ አይገባንም፡፡    

ነገር ግን የጌታችን ወንድም ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ እንዳስተማረን ሊያስጨንቀን የሚገባን ጉዳይ ከዚህ እንደሚከተለው ነው፡፡

 • “ምንት ይበቊዕ አኃዊነ ለእመቦ ዘይብል ሃይማኖት ብየ ወምግባረ ሠናይ አልብየ ቦኑ ትክል ሃይማኖቱ አድኅኖቶ (ወንድሞቻችን ሆይ እምነት አለኝ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ያዕ. ፪፥ ፲፬  በማለት በጥያቄ መልክ ካቀረበ በኋላ “ ሃይማኖትኒ እንተ አልባቲ ምግባረ ሠናይ ምውት ይእቲ ለሊሃ (ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው) ብሎ ስላስተማረን፡፡ ያዕ. 2፥ 18፡፡ ሃይማኖት ያለ ምግባር፤ ምግባር ያለ ሃይማኖት ዋጋ የለውም፡፡ ነፍስ የሌለው ሥጋ፤ ሥጋ የሌላት ነፍስ ሰው መባልን ሊያገኙ እንደማይችሉ ሁሉ ሃይማኖት/እምነት ያለው ምግባር ግን የሌለው እንዲሁም ምግባር ኑሮት እምነት/ሃይማኖት የሌለው ክርስቲያን ነኝ ባይ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥትም አይገባም፡፡ መልካም ምግባር ባለመኖሩ ሃይማኖቱ፤ እውነተኛ እምነት/ሃይማኖት ባለመኖሩ ምግባሩ ይፈርስበታል፡፡ በጎ ምግባር ከሌለው እምነቱ የሰይጣን እምነት ይባላል፡፡ አጋንንት ያምናሉ በጎ ምግባር ግን የላቸውም፡፡ ስለዚህ አይድኑም፤ያዕ. 2፥ 18-20።

በመሆኑም ከጥንት ከነቢያት ጀምሮ እስከ ዘመነ ሐዋርያት ድረስ በጎ ምግባር ብቻ ይበቃችኋል፤ ሃይማኖት አያስፈልጋችሁም ወይም ሃይማኖት ብቻ ይበቃችኋል በጎ ምግባር አያስፈልጋችሁም የተባለበት ዘመን የለም፡፡ ስለዚህ  ሃይማኖትን ከመልካም ሥነ-ምግባር ጋር አንድ አደርጎ መያዝ ነው፡፡ ዛሬ በዘመናችን እየደረሰብንና እየታየ ያለው መከራና ጭንቀት ሰው ሃይማኖት ከመልካም ሥነ- ምጋባር ጋር ይዞ ባለመገኘቱ ነው፡፡ 

በተለይም በአሁኑ ዘመን መልካም የሠራ ዋጋውን እጥፍ ድርብ የሚያገኝበት ጊዜ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያው ቃሉ ብታመም ጠይቃችሁኛል ያለውን ትእዛዝ በተግባር ፈጽሞ የሚከብርበት ዘመን ነው፡፡

 • “አማን እብለክሙ ኵሎ  ዘገበርክሙ ለአሐዱ እምእሉ አኃውየ ንኡሳን ሊተ ገበርክሙ (ከእነዚህ ከድኆች ወንድሞቸ ለአንዱ ያደረጋችሁለት ለእኔ አደረጋችሁልኝ ብዬ በእውነት እነግራችኃለሁ” ብሏል፡፡ 

“ወወደሶ ለዘገብረ ዘንተ” ለታመመ ሰው እርዳታ ያደረገውን ሰው ወደኔ ና ብሎ አመሰገነው፡፡ “ወአውረሶ” መንግሥተ ሰማያትን አወረሰው፤ “ወዘለፎ ለዘኢገብረ ዘንተ” እርዳታ ያላደረገውን ሰው ብታመም አልጠየቅኸኝም ብሎ ዘለፈው፤ ከርሱም አራቀው፡፡ ስለዚህ እኛን ሊያስጨንቀን የሚገባ ነገር በምንችለው ሁሉ ከእኛ የሚጠበቀውን ሳናደርግ እንዳንቀር ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ነቢየ እግዚአብሔር ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡-

 • “ብፁዕ ዘይለቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር (በደኃው በችግረኛው ላይ ያለውን ችግር አውቆ የሚሰጥ የሚመጸውት ሰው ንዑድ ክቡር ነው ከክፉ ቀን ያድነዋል ይሰውረዋልም) ያነሥኦ እግዚአብሔር በሕይወት ያነሣዋል” ይላል፡፡ 

ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደነገሩን የሚመጸውት ሰው “ወእመኒ ቦቱ ኃጢአት ይትኃደግ ሎቱ(ኃጢአትም ብትኖርበት ይሰረይለታል)”ሲሉ አረጋግጠው ነግረውናልና ካለን ሀብት፤ ገንዘብ፤ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ እውቀትና ጥበብ፤ መልካም ምክርና ርኅራኄ፤ የሃይማኖት ትምህርት  እንድናካፍል ታዘናል እንጂ እንደንጨነቅ አልተፈቀደልንም፡፡

በአጠቃላይ ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያው ቃሉ እስመ ጸሎት በሃይማኖት ያሐይዎ ለድውይ (አምኖ የሚጸልዩት ጸሎት የታመመውን ያድነዋልና) ወያነሥኦ እግዚአብሔር እግዚአብሔርም በሕይወት ያስነሣዋል  በተለይም “እስመ ለዝንቱ ዘመድ ኢይክሉ አውጽኦቶ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት (ሳይጾሙ፤ ሳይጸልዩ ይህን ሰይጣን ማስወጣት አይቻለውምና)”  በቅዱስ ቃሉ ስለነገረን በሃይማኖት፤ በጸሎት፤ በጾም፤ በምጽዋት፤በመልካም ሥነ- ምግባር ጸንተን ቸሩ እግዚአብሔርን ከሚደርስብን መከራ፤ ፈተና፤ ከታዘዘብን መቅሰፍት ሁሉ እንዲጠብቀን ልንለመነው እንጂ እንዲሁ ልንጨነቅ ስላላዘን ሕጉንና ትእዛዙን ተላልፈን የፍርድ ባለእዳዎች እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡

ሰአሊተ ምሕረት፤ አቊራሪተ መዐት፤ ወላዲተ አምላክ ሰአሊ ለነ ቅድስት!  

 

አባ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚ ሽን
ሊቀ ጳጳስ

https://www.facebook.com/EOTC.DICAC

‹ Back to List