Skip to main content

የፈተና ማለፊያ መንገዶች

28.04.2020 Media info Top news
የፈተና ማለፊያ መንገዶች

የፈተናን ማለፊያ መንገድ አውቆ በአግባቡ ተቋቁሞ ወደ ሕይወት ለመተርጐም የአመጣጥን ሁኔታ መረዳቱ ይጠቅማል፡፡ ፈተናን ታሸንፈው ዘንድ ልትከተላቸው የሚገቡ የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡

 

94636815_162047111934101_3379351251417300992_n

“ደካማ ይቅር አይልም፣ ይቅር ባይነት የጠንካሮች መለያ ነው” እንደሚባለው አንዳንድ ሰዎች የሚፈተኑበትን አሳቦች በማሸነፍ ለማለፍ ባለመቻላቸው የበደለኛነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ከመፈተን “ያለፍኩ” አይደለሁም ይላሉ፡፡ ተስፋ ይቆርጣሉ በመፈተናቸው ያፍራሉ፡፡ ይህ በክርስትና ሕይወት አለመብሰልና ነገሮችን በትክክል አለመረዳት ነው፡፡ “ታላቁ ክብራችን ያለመውደቃችን ሳይሆን በወደቅን ቁጥር መነሣታችን ላይ ነው”
በአንድ በኩል ፈተናን እንደ በጐ ነገር ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ክፉ ፈቃዱን በመፈጸም ላይ ያሉ ሰዎችን የራሱ ስለሆኑ ሰይጣን አይፈትናቸውም፡፡ ፈተና የድካም ወይም የዓለማዊነት ምልክት ብቻ ሳይሆን ሰይጣንም የሚጠላህ የመሆኑ ምልክት ነው፡፡ ሰው በመሆናችንና በወደቀው ዓለም በመኖራችን የሚመጡብን የነገሮች ክፍልም ነው፡፡ በመሆኑም በፈተና አትደነቅ፣ አትደንግጥ፣ ወይም እየሆነ ባለው ተስፋ አትቁረጥ፡፡ ፈተና አይቀሬ መሆኑና ሙሉ በሙሉ ልታስወግደው የማትችል ሰው መሆንህን ተገንዘብ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፡፡” 1 ቆሮ. 10÷13)
መፈተን ኃጢአት አይደለም፡፡ ፈተና ኃጢአት የሚሆነው በተሸነፍክበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ወፎች ከራስህ በላይ እንዳይበሩ ልትከለክላቸው አትችልም፡፡ ራስህ ላይ ጎጆአቸውን እንዳይሠሩ ለማድረግ ግን ትችላለህ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰይጣን የተለያየ የሚያስጨንቁ አሳቦችን እንዳያቀርብልህ ልትከለክለው አትችልም፡፡ ነገር ግን የሚያቀርብልህን አሳብ እምቢ ልትለው ግን ትችላለህ፡፡ (ዕብ.4÷5)
ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ በቀረብክ መጠን ሰይጣንም ይበልጥ ሊፈትንህ ይሞክራል፡፡ በእምነት የእግዚአብሔር ልጅ ስትሆን ሰይጣን እንደተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን መሪ ሊያጠፋህ ልብህን ይከፋፍለዋል፤ ፍርሃትና ጭንቀት ድንጋጤ ይለቅብሃል፡፡
አንዳንዴ በመጸለይ ላይ እንዳለህ ሰይጣን አሳብህ ባልሆነ መንገድ ሊያሳፍርህ በማቀድ ያልተለመደ ክፉ አሳብ ወደ አእምሮህ ያመጣል፡፡ ስለዚህ በድርጊቱ አትደናገጥ፣ አትፈር፡፡
የምትፈተንበትን ሁኔታ ለይተህ ካወቅህ ንቁ ሁን፡፡ ከሌሎች ይልቅ ለፈተና ይበልጥ የሚያጋልጡ አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ወዲያውኑ እንድትወድቅ ሲያደርጉህ ሌሎቹ ደግሞ ምንም አያስቸግሩህም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በተለይ በድካምህ የሚመጡ ስለሆኑ ለይተህ ልታውቃቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የሚያሰናክልህ ምን መሆኑን ሰይጣን በትክክል ስለሚያውቅ ወደ ሁኔታዎቹ ሊወስድህ ያለማቋረጥ ይተጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቀናል፡- “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ ንቁም ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሳ አንበሳ ወዲያና ወዲህ ይዞራል” መቼ እንደምትፈተን& በየትኛው ቀንና ሰዓት ፈተና እንደሚበዛብህ በየትኛው ቦታ ላይ እንደሆነ ማሰቡ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ፈተናን ለማለፍ የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልግህ ፈተናን ለማለፍ ያለህ ጽኑ እምነትና ሃይማኖት ፈተናን ሊያሳልፍልህ የሚችለው የአምላክህ ርዳታም ጭምር ነው፡፡
ፈተና ይመጣል ብለን እንድንጠብቅና እንደ አመጣጡ ለመጋፈጥ እንድንዘጋጅ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በመደጋገም ይነግረናል፡፡ (ማቴ. 26÷41፣ ኤፌ. 6÷10-18፣ 1ተሰ. 5÷6 1ጴጥ. 1÷13፣ 5÷8)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- “ለዲያብሎስ ሥፍራ አትስጡት” (ኤፌ. 4÷28) ብሏል፡፡ በብልሃት ማቀድ ፈተናን ይቀንሳል፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ እንዲህ የተባለውን ምክር እንከተል፡- “የእግርህን መንገድ አቅና አካሄድህም ሁሉ ይጽና” “የቅኖች ጐዳና ከክፋት መራቅ ነው፤ መንገዱን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል” (ምሳ.16÷17)

ፈተናን ለማለፍ ራስን መግዛት

እግዚአብሔር በማንኛውም ጊዜና ወቅት አስቸኳይ ጥሪ የመቀበያ ልዩ መስመር አለው፡፡ ፈተናን ለመቋቋም ርዳታ ትጠይቀው ዘንድ ስለሚፈልግ እንዲህ ብሏል፡፡ “በመከራ ቀን ጥራኝ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ" (መዝ. 50÷15)፤ ይህም ጸሎት አምላክህ ደራሽ እንደሆነ ይገልጽልሃል፡፡ እባክህ ድረስልኝ? አድነኝ? ርዳኝ? የሚለው ጸሎት ፈተና በድንገት ሲያጠቃህ ወደረዳትህ እና አምላክህ የምትማፀንበት የርዳታ ጥሪ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የድረስልን ጩኽታችንን የሚሰማው ድካማችንን የሚረዳና የሚራራልን በመሆኑ ነው፡፡ “ነገር ግን እግዚአብሔር የሚወዳችሁ ልጆቹ እንደመሆናችሁ መጠን እርሱን ምሰሉ” (1ዮሐ. 3÷1)፡፡
እግዚአብሔር ፈተናን እንድናሸንፍ ሊረዳን በመጠባበቅ ላይ ከሆንን ፊታችንን ወደ እርሱ የማንመልሰው ለምንድነው? እውነቱን እንናገር፣ አንዳንድ ጊዜ ርዳታ አንሻም፤ ስህተት መሆኑን ብናውቅም በፈተና መሸነፍን እንፈልጋለን፡፡ ይህን የምናደርገው እግዚአብሔር ለእኛ ከሚያውቀው ይልቅ ራሳችን የሚሻለንን እናውቃለን ብለን ስለምናስብ ነው፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ በተመሳሳይ ኃጢአት በተደጋጋሚ በመሸነፍ ላይ ስለምንገኝ የእግዚአብሔርን ርዳታ ለመጠየቅ እናፍራለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ፍጹም አይታክትም፣ አይሰለችም፣ በተደጋጋሚ ወደ እርሱ በመጮሀችን ምክንያት ትዕግሥቱ አያልቅም፡፡ “እንግዲኸ ወደጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ”፡፡ (ዕብ. 4÷16)፡፡
ፈተናዎች የበለጠ በሃይማኖት እንድንጸና እና እንድናምን ያደርጉናል፡፡ አንድ ዛፍ ነፋስ በነፈሰበት ቁጥር ሥሮቹ እየበረቱ እንደሚሄዱ ፈተናን በተቋቋምክ ጊዜ ሁሉ ይበልጥ እውነተኛ ክርስቲያን ትሆናለህ እንጂ በምትሰናከልበት ጊዜ አስከፊ ፍጻሜ ላይ ደረስክ ማለት አይደለም፡፡ ያኔ ከመሸነፍ ወይም ተስፋ ከመቁረጥ ወደ እግዚአብሔር ተመልከት፤ ርዳታውን ጠብቅ ፤ የኋላ ሽልማትህን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን አስታውስ፡ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው ምክንያቱም ፈተና ይቋቋም ዘንድ እግዚአብሔር ለሚወዱት የሰጠውን ተስፋ የሕይወትን አክሊል ያገኛል፡፡” (ያዕ 1÷12) ፈተናን ለማለፍ ከክñ ምኞት ሽሽ በንፁሕ ልብ ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን ተከተል፡፡
(1ኛ ጢሞ 2÷2)
በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገስ እንድትችሉ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፈተና ልትሸከመው ከምትችለው በላይ የከበደ መስሎ ይሰማህ ይሆናል፡፡ ይህ ከሰይጣን የሚመጣ ሐሰት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈተናን ትቋቋምበት ዘንድ ውስጥህ ካኖረው አቅም የበለጠ ፈተና እንዲደርስብህ እንደማይፈቅድ ቃል ገብቷል፡፡ ሰይጣን ሊፈትንህ ሲፈልግ እግዚአብሔር ደግሞ የማታሸንፈው ማንኛውም ፈተና እንዲደርስብህ አይፈቅድም፡፡ “ንጹሕ ሰው ሆኖ መከራ የደረሰበት ቅን ሰው ሆኖም የተደመሰሰ አይተህ ታውቅ እንደሆነ እስቲ ወደ ኋላ መለስ ብለህ አስብ” (ኢዮ. 4÷7)፡፡
-----------------------------------//-----------------------------------------
አባ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን
ሊቀ ጳጳስ

www.eotcdicac.org

https://www.facebook.com/EOTC.DICAC

‹ Back to List